ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም በ አክራሪዎች ላይ እጄን አጣጥፌ አልቀመጥም አለ

በየመስጊዱ ሕዝበ ሙስሊሙ የዓርብ ፀሎትን በሰላም እንዳይፀልይ በማወክ በግልጽና በህቡዕ የሚንቀሳቀሱ አካላት በሃይማኖት ሽፋን ሰላም ከማደፍረስ የማይቆጠቡ ከሆነ፣ እጁን አጣጥፎ እንደማይመለከት መንግሥት አስገነዘበ፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶ/ር ሽፈራው ተክለ ማርያም የመሥርያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ በግልጽና በህቡዕ በመንቀሳቀስ የአገሪቱን ሰላምና ልማት የሚያውኩትን ፀረ ሰላም ኃይሎች መታገስ ሰላም ወዳዱን ሕዝብ ለአደጋ ማጋለጥ ነው፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ሕዝበ ሙስሊሙ እነዚህን አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች እንዲመክራቸው፣ እንዲገስጻቸውና ለይቶ በማጋለጥ የተለመደ ትብብር እንዲያደርግ እያሳሰብን፣ እነዚህ አካላት በሃይማኖት ሽፋን ሰላማችን ከማደፍረስ የማይቆጠቡ ከሆነ መንግሥት እጁን አጣጥፎ እንደማይቀመጥ ማስገንዘብ ይፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በእስልምና ሃይማኖት ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ጥቂት አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝበ ሙስሊሙን በማደናገር፣ በመደለልና በማስፋራራት የአክራሪነት እንቅስቃሴያቸውን በይፋ ማራመድ መጀመራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ እነዚህ ኃይሎች በተለይም አዲስ አበባን እንደ ማዕከል በመጠቀም በኦሮሚያና ሌሎች አንዳንድ አካባቢዎች የአክራሪነት ፍላጐታቸውን በግድ ለመጫን እየተንቀሳቀሱ መሆኑን፣ ባይሳካላቸውም ሕዝበ ሙስሊሙንና መንግሥትን ለማጋጨት አልመው ጋዜጦችን፣ መጽሔቶችንና የተለያዩ ኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም የተለያዩ ማደናገሪያ አጀንዳዎችን በማስተጋባት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ለሕዝበ ሙስሊሙ ባለው ጥልቅ እምነትና ከበሬታ፣ እንዲሁም የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ባለው ዝግጁነት በአወሊያና በእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጉዳይ ጥያቄ አለን ብለው መንቀሳቀስ የጀመሩ ግለሰቦችን ሲያወያይ እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ሽፈራው፣ የእነዚህ ወገኖች ጥያቄ ማጠንጠኛ የነበረውን የሕዝበ ሙስሊሙን ተቋም የሆነውን የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በተያዘለት የድርጊት መርሐ ግብር መሠረት ሕዝበ ሙስሊሙን በሰፊው በሚያሳትፍ መንገድ እንዲፈጸም ድጋፍ እንደሚያደርግ መንግሥት ቢገልጽም፣ ጥያቄ አለን በሚሉ ግለሰቦች ውስጥ የተሸሸጉና ከእነሱም በስተጀርባ ድብቅ የትርምስ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ግለሰቦች ሕዝበ ሙስሊሙን በማደናገር ላይ እንደሚገኙ አስታውቀዋል፡፡ እርሳቸው እንዳሉት፣ በመንግሥት በኩል እነዚህ ጥቂት አክራሪ ግለሰቦችና ቡድኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ መንገድ ተከትለው እንዲጓዙ ያልተቋረጠና ያልተቆጠበ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡ መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት ያለበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ የዜጐቹን ሰላም ወዳድነት በመተማመንና የአክራሪ ፀረ ሰላም ኃይሎቹ ማንነትና ድብቅ ፍላጐት በሕዝቡ ውስጥ በግልጽ እስከሚታወቅ ድረስ በትዕግስት ጠብቋል ብለዋል፡፡
Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular