በ አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው ሰላሃዲን(ሐጂ የኑስ) መስጂድ የተዘጋጀው ያልተሳካው የመጅሊስ ሴራ

By Zain Usman

ከህዝብ እውቅና የተነፈገው እና ህዝብ ፊት የነሳው መጅሊስ እተፋፋመ የመጣውን የህዝበ-ሙስሊሙ ተቃውሞ ለማኮላሸት ካዘጋጃቸው ሴራዎች በህዝበ-ሙስሊሙ ጥረት ከሸፈ፡፡

 

ህዝበ ሙስሊሙ ያነገባቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ማሰማት ከጀመረ ስድስተኛ ሳምንቱን በያዘበት በዚህ ሳምንት የህዝቡ እንቅስቃሴ እንቅልፍ የነሳቸው የመጅሊስ አመራሮች አዲስ እና ጊዜ ማራዘሚያ ይሆናል በማለት ያዘጋጁትን ዘዴ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ አደረጉ፡፡ መጅሊስ የመስጂድ ኢማሞችን ከሰበሰበ በኋላ የጁምዓ ኹጥባቸውን በአህባሽ አስተምህሮት ዙሪያ እንዲያደረጉ፣ ቅዳሜና እሁድ ደግሞ የአካባቢውን ህዝብ በመጥራት እንዲያስተምሩ ቀጭን ተእዛዝ አስተላለፈ፡፡ ፅንፈኞች እና አክራሪዎች ህዝቡን ለማወናበድ የሚያደርጉት ሙከራ እንጂ አህባሽ እና አስተምህሮቱ ባእድ እንዳልሆነ  በመሆኑም ህዝቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ምክር አዘል ተግሰፅ ለማስተላለፍም ተስቦ ነው፡፡ ይህ ተልዕኮ ከተሰጣቸውና ተግባራዊ ከሚያደርጉት ውስጥ በተለምዶ ኳስ ሜዳ በሚባለው አካባቢ  የሚገኘው ሰላሃዲን(ሐጂ የኑስ) መስጂድ አንዱ ነበር፡፡ የመስጂዱ ኢማም ባይሆኑም ዘወትር የጁምዓ ኹጥባ በማድረግ የሚታወቁት ሽኽ ---- የትላንትናውን(10/02/2012) የጁምዓ ኹጥባ ተከትሎ ነገ ቅዳሜ(11/02/2012) በዚሁ መስጂድ ስለ አህባሽ ትምህርት እንደሚሰጥና ህዝቡም እንዲታደም ማስታወቂያ ተናገሩ፡፡

የቀጠሮው ሰዓት ከጧቱ 2፡30 ቢሆንም እስከ 4፡00 ድረስ ቀጠሮውን አክብረው በበቦታው የተገኙ ሰዎች ቁጥር ከ20 እምብዛም የዘለቀ አልነበረም፡፡የነበረው አማራጭ ባለው የታዳሚ ቁጥር መጀመር ነበርና ኡኹዋን አስመልክቶ ከኻጢቡ አንደበት የፈለቁት ቃላት ከመድረክ ወደ ታዳሚው መወርወር ጀመሩ፡፡ ወሬያቸው እየሞቀ ሲመጣ የታዳሚውን ትግስት የተፈታተነው ነገር ብልጭ አለ፡፡ ከታዳሚዎቹ አንዱ ከተቀመጠበት ተነስቶ ሲያበቃ ‹‹የተጠራነው ስለ አህባሽ ትምህርት ሊሰጥ ሆኖ ሳለ ለምን ወደ ጉዳዩ አንገባም?›› ሲል ጠየቀ፡፡ ሼኹም በወሰዱት ስልጠና መሠረት ስለ አህባሽ መናገሩን ቀጠሉ፡- ‹‹አህባሽ የሚለው ቃል ሀበሻ ከሚለው የተነሳ ሲሆን ስሙንም ጥላቻ ያለባቸው ሰዎች አመጡት እንጂ ሼኽ ዓብደላህ ሐረሪ የሚያስተምሩት ትምህርት ስህተት የለውም እና…›› እያሉ መናገራቸውን ሲቀጥሉ ታዳሚዎች መጠየቅ ሚፈልጓቸው ነገሮች እንዳሉ መናገር ጀመሩ፡፡ ሼኹ ግን ጥያቄዎችን በመቃወም ንግግራቸውን ቀጠሉ፡፡ በዚህ መሃል ከታዳሚዎች አንዱ በያዘው ሞባይል ቀረፃ ለማድረግ ተነሳ፡፡ ሼኹ አስተውለውት ኖሮ ቁጣቸው ገንፍሎ በመውጣት ሁኔታው ፈሩን መልቀቅ ጀመረ፡፡ የመድረኩ ሁኔታ በዚህ መንፈስ መቀጠል ባለመቻሉ ፍትጊያው ከመጠንከሩ በፊት ሰዎች ተረባርበው ነገሩን ካበረዱት በኋላ ሼኹን ከለላ በመስጠት ከመስጂዱ አስወጧቸው፡፡ በአከባቢው ለሚገኙ የጥበቃ አካላት ካስረከቧቸው በኋላ በታክሲ ወደ ቤታቸው እንዲሸኙ ሆኗል፡፡ ሆኖም በዚህ ሁኔታ የተጠናቀቀው መድረክ በወደፊቱ የመስጂዱ ሁኔታ ላይ አደጋ ማንዣበቡ ያሳሰባቸው የመስጂዱ የጀመዓ አባላት እርስ በርስ ተሰባስበው ሲያበቁ ምን እናድርግ ሲሉ ውይይት ጀመሩ፡፡በዚህ ሁኔታ ላይ እያሉ አንድ ግለሰብ ድንገት ከውጭ መጥቶ ሹራውን ተቀላቀለ፡፡ይህ ሰው በዚህ መስጂድ ጀመዓ ብዙም የታወቀ አይደለም፡፡ነዋሪነቱ ቀበሌ 14 የሆነው ግለሰብ አልፎ አልፎ በዚህ መስጂድ እየመጣ ይሰግዳል፡፡ የሹራ አባላቱ ሰውዬው ከመምጣቱ አስቀድሞ እንደነበረው ሹራቸውን መቀጠል አልቻሉም፡፡ ‹‹የምትናገሩትና የምታወሩት ነገር ትክክል አይደለም›› በማለት በተደጋጋሚ ሹራውን ማወክ ጀመረ፡፡ እንዲወጣ ቢፈልጉም ከመስጂደድ ኮሚቴዎች አንዱ ሰውዬ አውቀዋለሁ በማለቱ ጉዳዩ ይበልጥ ስላማይመለከተው ተነግሮት አርፎ እንዲቀመጥ አዘዙት፡፡ ተልዕኮ ያለው የሚመስለው ይኸው ግለሰብ መረበሹን ቀጠለ፡፡ ሁኔታው በዚህ ሁኔታ እንዳይቀጥል ለማድረግ ሲባል ሰውዬውን እንደሼኹ ለጥበቃ አካላት ሰጥተው ለመሸኘት ቢሞከርም ሁኔታው መልኩን ወደ አልተፈለገ አቅጣጨ ቀየረ፡፡ ግለሰቡ እሰጥ አገባ ውስጥ ገባ፡፡ ድብድብ ተጀመሮ ሁኔታው ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ግለሰቡ ሮጦ ለማምለጥ ሲሞክር ከኪሱ አንድ ወረቀት ወደቀ፡፡ ይህ ወረቀት ‹‹ተልዕኮ የተሰጠው ግለሰብ ስም ------------›› የሚል ርዕስ ያለው ሆኖ ተገኘ፡፡ በዚህም አሳፋሪው ተልዕኮ ሳይሳካ በሙስሊሞቹ የጠነከረ የአንድነት ክንድ ሳይሳካ ቀረ፡፡ በዚህ መስጂድ የነበረው የመጅሊስ ተልዕኮ በጠቅላላ ከሸፈ፡፡አልሐምዱሊላህ፡፡

በሙስሊሞች የተባበረ የአንድነት ክንድ ኮርተናል፡፡

 

አታላዮች አይደለንም አታላዮች ግን ፈፅሞ አያታልሉንም! 

Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular