የአወሊያ የህዝብ ንቅናቄን ተከትሎ የተቋቋሙ ኮሚቴ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ባካሄደው ውይይት ተስፋ ሰጪ ምላሽ ማግኘቱን ገለፀ

ጥር 21/2004 ላለፉት አራት ተከታታይ የጁመዓ ሰላቶች በአወሊያ የተካሄደውን የህዝበ ሙስሊሙ ጠንካራ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ተከትሎ የተቋቋመው መፍትሔ አፈላላጊ ኮሚቴ ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በተካሄደው ውይይት ተስፋ ሰጪ ምላሽ ማግኘት መቻሉን አስታወቀ፡፡ ኮሚቴው ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር የሚያካሄደውን ውይይት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልና የፊታችን ረቡዕ ቀጣይ ውይይት ለማድረግ የሚያስችለውን ቀጠሮ እንደያዘም አመልክቷል፡፡ ኮሚቴው በአወሊያ ሰሞኑን በተከታታይ የተካደውን ጠንካራ የሕዝብ ንቅናቄ ተከትሎ ነው የተቋቋመው… በትዕይንተ ሕዝቡ ተሳታፊ በሆኑ የአዲስ አበባ ሙስሊሞች ኮሚቴው ሲሰየም ስድስት አባላትን ያካተተ ነበር፡፡ ባለፈው ጁመዓ ደግሞ አቅሙን አጠናክሮ ወደ 16 አባላትን በማቀፍ መፍትሔ ማፈላለግ ስራውን ተያይዞታል፡፡ ወጣት ዳዒያንን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን፣ ዑለሞችንና ተሰሚነት ያላቸውን ተዋቂ ምሁራንን ያሰባሰበው ይኼው ኮሚቴ ለሚሊዮኖች ቅሬታ ዘላቂ መፍትሔ የማፈላለግ ኃላፊነቱን ከተረከበ ከሳምንት ያለፈ ዕድሜ የለውም፡፡ ሆኖም በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ ከኮሚቴው አባላት መካከል ዘጠኙ የተሳፉበትን ውይይት ከሁለት የመንግስት ከፍተኛ ባስልጣናት ጋር ማካሄድ ችለዋል፡፡ ውይይቱ የተካደው ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትር ዶክተር ሽፈራው ተ/ማሪያምና ከሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ጋር ሲሆን ለሶስት ሰዓታት ያህል የዘለቀ ነበር፡፡ የኮሚቴው አባላት ለሚኒስትሮች ያነሷቸው ነጥቦች በሶስት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ እንደሆኑም በውይይት ተሳታፊ የነበረው ዳዒ ያሲን ኑሩ ይናገራል፡፡ የመጅሊስ አመራር ምርጫ ይካሄድ፣ የአህባሽ ቡድን አስተምህሮትና ጫና ይቁም፣ የመንግስት የኃይማኖት ጣልቃ ገብነት ይቁም፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየተተገበረ ያለው መመሪያ የህዝበ ሙስሊሙን ነፃነት ይጋፋልና ይስተካከልል የሚሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ የአወሊያ ኢስላማዊ ማዕከል የህዝብ ነውና ሕዝባዊነቱን ጠብቆ ይተዳደር የሚለውን ነጥብ ጨምሮ ሁለቱም ሚኒስትሮች በኮሚቴው አባላት ገለፃ ተደርጎላቸዋል፡፡ በተነሱት ሕዝባዊ ቅረታዎች ዙሪያ ከሚኒስትሮች መፍትሔ ለማፈላለግ የሚረዳ ተስፋ ሰጪና በጎ ሊባል የሚችል ምላሽ መገኘቱን ዳዒ ያሲን ኑሩ ገልፆልናል፡
Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular