የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪዎችን ለመምረጥ ዝግጅት እያደረጉ ነው

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች መሪዎችን ለመምረጥ ዝግጅት እያደረጉ ነው ሰኔ ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም ኢሳት ዜና:-ሙስሊሞቹ መንግስት በየቀበሌው ለማድረግ የሰበውን የመጅሊስ ምርጫ እንደማይቀበሉትና ምርጫውን በራሳቸው መንገድ በመስኪዶች ውስጥ ለማድረግ እንቅስቃሴ ጀምረዋል። ሙስሊሞቹ በራሳቸው መንገድ ተጉዘው የመጅሊስ አባላትን የሚመርጡ ከሆነ፣ በመንግስት ተደግፈው ወደ ስልጣን ከሚመጡት የመጅሊስ አባላት ጋር ውዝግብ የሚፈጠር ይሆናል። መንግስት የመጅሊስ አባላትን ለማስመረጥ የሚያደርገው ጥረት ሙስሊሞችን እያስቆጣ መምጣቱንም ዘጋቢአችን ከአዲስ አበባ ገልጧል። በመንግስትና በሙስሊሞች መካከል ያለው ውዝግብ እየጨመረ መምጣቱን ተከትሎም የመንግስት የደህንነት ሀይሎች በእንቅስቃሴው መሪዎች ላይ የማስፈራራት ዘመቻ ከፍተዋል። ይህን ተከትሎም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ችግሮች መፍትሄ አፈላላጊ ጊዜያዊ ኮሚቴ በመንግሥት የደህንነት ሰዎች ከበባ ውስጥ መግባታቸውን በመግለጥ እነሱ ቢታሰሩ እንኳ ህዝበ ሙስሊሙ ሰዋዊ እና ሕገ-መንግሥታዊ መብቱን ለማስከበር ተተኪ የኮሚቴ አባላትን እንዲመርጥ አሳስበዋል፡፡ በአወሊያ መስኪድ ከአምስት ወር በፊት የተቋቋመው ጊዜያዊ ኮሚቴ ሰሞኑን በሲዲ በበተነው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደገለጸው የህዝበ ሙስሊሙ ሠላማዊ የመብት ጥያቄ ወደ ፊት መቀጠል እንጂ በመንግሥት አሻጥር ወደ ኋላ መቀልበስ የለበትም ብለዋል፡፡ ለዚህም ህዝበ ሙስሊሙ ከወዲሁ የመብት ጥያቄውን ሊያስቀጥሉለት የሚችሉ አዳዲስ የኮሚቴ አባላትን በመጪው ዓርብ በየመስኪዶቹ እንዲመርጡ ያሳሰበ ሲሆን ተግባራዊ ለማድረግም በዝግጅት ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡ ዘጋቢያችን ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በአዲስ አበባ በሚገኙ መስኪዶች የመብት ጥያቄውን ሊያስቀጥሉ የሚችሉ አቅጣጫ መሪዎችንና የአዲስ አበባ እና የክልል የእስልምና ምክር ቤት የ/መጅሊስ/ አመራሮችን ለመምረጥ የሚያስችሉ የአስመራጭ ኮሚቴ ለማዋቀርና እጩ ተመራጮችን ለመመልመል በዝግጅት ላይ ሲሆኑ በመጪው ዓርብ ተግባራዊ ይደረጋል በማለት ገልጸዋል፡፡ በአንፃሩ የኢህአዴግ መንግሥት የአዲስ አበባ እስልምና ምክር ቤት /መጅሊስ/ ምርጫን በቀበሌና በወረዳ መዋቅር በመንግሥት ባጀት ለማከናወን በመጪው ሰኔ 13 እስከ 15 2004 ዓ.ም በዑላማዎች ምክር ቤት በኩል ለማስፈጸም የራሱን ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ይህንን የመስኪድ ምርጫ ለማስቀረት ነው ሰሞኑን የደህንነት ኃይሎች የኮሚቴ አባላቶች ላይ ከበባና ክትትላቸው ያጠበቁት ሲሉ አንድ የኮሚቴ አባል ለዘጋቢያችን አስረድተዋል፡፡ በኮሚቴው ላይ የሚካሄደው የፕሮፓጋንዳ ዘመቻም ተጠናክሮ ቀጥሎአል። አዲስ ዘመንን የመሳሰሉ በህዝብ ግብር የሚተዳዳሩት ጋዜጦች የሙስሊሙ መሪዎች ከግንቦት7 እና በውጭ አገር ከመኖሩ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ እምነት አባቶች ጋር ቁርኝት እንዳለቸው የሚገልጡ ጽሁፎችን ይዘው እየወጡ ነው። የሙስሊም መሪዎችን ከግንቦት7 ጋር ለማያያዝ የተፈለገው ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት በአሸብሪነት ከሶ ለመምታት የታቀደው እቅድ፣ በህዝብ ዘንድ ድጋፍ አያገኝም በማለት መሆኑን አንድ ስማቸው እንዳይገለጥ የፈለጉ የሙስሊም ጋዜጣ አዘጋጅ ገልጠዋል። ታዋቂዎችን የሙስሊሙን አመራሮች ከአልቃይዳ ወይም ከሌሎች የእስልምና ድርጅቶች ጋር አያይዞ መፈረጅ በአለማቀፍም ሆነ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ተቀባይነትን የሚያገኝ ባለመሆኑ፣ በፓርላማው አሸባሪ የሚል ስም የተሰጠውን ግንቦት7ትን ስም በመጥቀስ መሪዎችን ለመምታት መታቀዱን በመንግስት ጋዜጦች የሚወጡ ጽሁፎች ያሳያሉ ብሎዋል።
Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular