AHBASH & SUFIYA

አህባሽ እና “ሱፊያ” ኡባህ አብዱሰላም ሰዒድ (I want all of you to compare this article with what “Majlis” and Alquds says about “Sufi”) በቅርቡ የአንድ ታላቅ መስጊድ ኢማም በሱፊያ ላይ ያተኮረ ኹጥባ ማድረጋቸውን ሰማሁ፡፡ ታዲያ አንዳንድ የፌስቡክ ጓደኞቼ ኢማሙ “እኛ ወሀቢዎች አይደለንም፤ እኛ ሱፊ ነን፤ አሁን ጊዜው የሱፊያ ነው፤ ሱፊያ ደግሞ የሰሀባዎችና የነቢያችን መንገድ ነው፤ ወዘተ...” ብለው ተናግረዋልና ስለዚህ ጉዳይ የምታውቂው ነገር ምን አለ?” የሚል ጥያቄ አቀረቡልኝ፡፡ በሰማሁት አባባል በእጅጉ ተገረምኩ፡፡ አዘንኩ!! ምን እንደማደርግም ግራ ገባኝ፡፡ ኢማሙ እንዲህ አይነት ተራ ንግግር በኹጥባ ላይ ማድረጋቸውን ለማመን ቢከብድም በራሴ መንገድ ባደረግኩት የማጣራት ሙከራ ነገሩ እርግጥ መሆኑን ተረዳሁ፡፡ በሌላ በኩል ለነዚያ ጓደኞቼ የሚሆን ምላሽ በዚያች ቅጽበት መስጠቱ ከበደኝ፡፡ ምክንያቱም የተሰውፍ መጽሀፍት በአጠገቤ የሉም (መካሺፉል ቁሉብ ከሚለው የኢማም አቡ-ሐሚድ አል-ገዛሊ መጽሀፍ በስተቀር)፡፡ በኢንተርኔት ላይ በተሰውፍ ስም የተለቀቁ ዌብሳይቶች ደግሞ ከጥቂቶቹ በስተቀር ምንም እምነት የሚጣልባቸው አይደሉም፡፡ ነገር ግን አህባሽ ሙስሊሞችን ከሚያጭበረብርባቸው ዘዴዎች አንዱ “እኛ ሱፊዎች ነን” የሚለው ፕሮፓጋንዳ እንደሆነ ስለማውቅ ዝም ከማለት የቻልኩትን ያህል ልጻፍላቸው በማለት ተነሳሁ፡፡ ወደ ዋናው ጽሁፍ ከመግባታችን በፊት ግን መጠነኛ ማሳሰቢያ አለኝ፡፡ ይህንን ጽሁፍ ስጽፍ መነሻ የሆነኝ በአብዛኛው ድሮ ካነበብኩት ሀሳብ የተረፈኝ መጠነኛ እውቀት እንጂ በቅርብ ጊዜ ያነበብኩት መረጃ አይደለም፡፡ ስለዚህ የመረጃ ክፍተት ሊኖር እንደሚችል አምናለሁ፡፡ የጽሁፌን መልእክት ለማገናዘብ የሚፈልግ አንባቢያ ሰይድ አቡል-አእላ መውዱዲ የጻፉትን Towards Understanding Islam፤ አቡል ሐሚድ አል-ገዛሊ የጻፉትን አል-ኢሕያእ ኡሉሙድዲን እና መካሺፉል ቁሉብ፣ ሼኽ አብዱልቃዲር አል-ጄይላኒ የጻፉትን “አል-ጉንያ ሊጣሊብ ጠሪቀል ሐቅ”፣ ታዋቂው ገጣሚ ፈሪዱዲን አጣር የጻፈውን “ተዝኪራቱል አውሊያ” ወዘተ.. የመሳሰሉ መጽሀፍትን መመርመር ይችላል፡፡ ተሰውፍ “ተሰውፍ” (Sufism) በጥሬ ትርጉሙ “ሱፍ መልበስ” ማለት ነው፡፡ በተገቢው መንገድ ሲተረጎም ግን “የልብ ጥራት” ማለት ነው፡፡ ሙስሊም የሆነ ሰው ልቡ በአካሉ ከሚያደርገው ኢባዳ ጋር በእኩል ሁኔታ እንድትራመድለት ሲፈልግ ልዩ ልዩ ጥበባዊ ዘዴዎችን የሚማርበት መንገድ ነው- “ተሰውፍ”፡፡ ይህም ልብን ከልዩልዩ የልብ በሽታዎች ማጥራት ማለት ነው፡፡ በቁርአንና በሀዲስ በስፋት እንደተገለጸው ሰዎች ከፈጣሪ ጋር ያላቸውን ትስስር የምታበላሽባቸው አንዲት አካል አለች፡፡ እርሷም ልብ ናት፡፡ ሙእሚኖች ቁርኣናዊ ግዳጃቸውን በተገቢው መንገድ ለመወጣት ከፈለጉ ልባቸውን ከበሽታ ማጥራት አለባቸው፡፡ በሌላ በኩል ፈጣሪያችን አላህ (ሱ.ወ.) ለምንሰራቸው መልካም ስራዎች የሚከፍለንን ምንዳ (አጅር) የሚወስነው የልባችንን ጥራት በመመዘን ነው፡፡ በከፍተኛ የልብ ጥራት የአንድ ብር ሰደቃ የሰጠ ሰው ከፍተኛ ሽልማት አለው፡፡ ሰውየው መካከለኛ የልብ ጥራት ካለው ሽልማቱ ያንስበታል፡፡ የልብ ንጽህናው በጣም የጎደፈ ሰው ደግሞ ሽልማቱ እጅግ ዝቅተኛ ነው (ሰውዬው መቶ ብር ቢሰጥ እንኳ በንጹህ ልብ አንድ ብር የሰጠውን ሰው ያህል ሽልማት አያገኝም)፡፡ ልቡ ሙሉ በሙሉ የቆሸሸ ሰው ግን ከአላህ ዘንድ ምንም ሽልማት አያገኝም፡፡ እንግዲህ ይህንን የልብ ጥራት ማምጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ኡለማ ለዚህ ጥያቄ የሚሆን ምላሽ ሲፈልጉ ነው “ተሰውፍ” የሚባለው አስገራሚ (አንዳንድ ጊዜ አወዛጋቢ) ኢስላማዊ የትምህርት ዘርፍ የተወለደው፡፡ ተሰውፍን እንደ አንድ የትምህርት ዘርፍ አድርጎ ማስተማር መቼ እንደተጀመረ በትክክል አይታወቅም፡፡ በርካታ ምንጮች ታዋቂዎቹን የበስራ ምሁራን ሐሰን አል-በስሪንና ራቢአቱል አደዊያን እንደ ጀማሪዎች ይጠቅሳሉ፡፡ ለመጀመሩ ሰበብ የሆነውም በጊዜው የነገሰው የልዩ ልዩ ፊርቃዎች (ሺዓ፤ ኻዋሪጅ፤ ሙርጂአ፤ ጀሀሚያ፤ ሙእተዚላ፤ ቀደሪያ፤ ጀብሪያ ወዘተ…) ሽኩቻ እንደሆነ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ በተሰውፍ ላይ የሚያተኩሩ መጽሀፍት መጻፉንም ማን እንደጀመረው በርግጥ አይታወቅም፡፡ እንደሚመስለኝ ከሆነ የተሰውፍ መጽሀፍት መጻፍ የጀመሩት ከሂጅራ በኋላ በ4ኛው መቶ አመት ገደማ፤ ማለትም እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ900 አ.ል. በኋላ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በ10ኛው፤ በ11ኛውና በ12ኛው ክፍለ ዘመናት ፈሪዱዲን አጣር፤ አቡ ሀሚድ አል-ገዛሊ፤ አህመድ አል-ሪፋኢ፤ ሼኽ አብዱልቃዲር አል-ጁይላኒ ወዘተ… የመሳሰሉ ምሁራን በተሰውፍ ላይ ያተኮሩ በርካታ መጽሀፍትን አበርክተዋል፡፡ ተሰውፍና የልብ በሽታዎች ልባችን የሚቆሽሸው በተለያዩ በሽታዎች ነው፡፡ እነዚህ የልብ በሽታዎች ያሉበት ሰው ኢባዳውን በወጉ አያደርግም፡፡ ውሎውና ድርጊቶቹ ከኢስላማዊ አዳብ ጋር አይገጥሙለትም፡፡ ከግለሰቦችና ከማህበረሰቡ ጋር ያለው ግንኙነትም የተስተካከለ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በዚህች አለም ብቻ ሳይሆን በወዲያኛውም አለም ታላቅ አደጋን ያስከትልበታል፡፡ ስለዚህ ከአደጋው ለመዳን ልቡን ከበሽታ ማጥራት ይጠበቅበታል፡፡ የሰውን ልብ ከሚያደርቁትና ኢማንን ከሚያጎድሉት በሽታዎች መካከል የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ኒፋቅ፡- የሙናፊቅነት ስሜት ጡግያን፡- ጥመት ኪብሪያእ፡-ኩራት ጁብር፡ ትዕቢት ሪኣእ፡- ልታይ ልታይ ማለት ዘን፡- ከንቱ ጥርጣሬ ገፍላን፡- መሰላቸት ሻህዋእ፡- ከገደብ ያለፈ ስጋዊ ፍላጎት ወዘተ… አላህና መልዕክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) ከነዚህ በሽታዎች እንድንጠቀቅ አስተምረውናል፡፡ የተሰውፍ ሰዎች ለነዚህ በሽታዎች የሚሆኑ መድሃኒቶችን ነው የሚያስተምሩት፡፡ የነዚህ መድሃኒቶች ምንጭ ቁርአንና ሱንና ነው፡፡ ልቡን ከነዚህ በሽታዎች ያጠራ ሰው ዒባዳውን በታላቅ ኹሹእ (የአላህ ፍራቻ) ማከናወን ይችላል፡፡ በተሰውፍ ከምንታከምባቸው መድሀኒቶች መካከል ከሁሉም የሚበልጠው “ዚክር” (አላህን ማስታወስ ) ነው፡፡ ቁርኣን “ልቦች በዚክር ይረጥባሉ” በማለት ምስክርነቱን ሰጥቷልና!! እንግዲህ “ሱፊ” የሚባል ሰው ልቡን ከበሽታ ለመጠበቅ ሲል የተሰውፍን ጥበብ የሚከተል ማለት ነው፡፡ ይህ የተሰውፍ ጥበብ ደግሞ ከቁርአንና ከሀዲስ ጋር የማይጋጭ መሆን አለበት፡፡ በተጨማሪም ሰውየው ሌላውን ኢባዳ ትቶ ተሰውፍን ብቻ የሙጥኝ ብሎ መያዝ አይችልም፡፡ “ተሰውፍ” ሰውዬው በኢባዳ ላይ ብርቱ ሆኖ እንዲቆይ የሚረዱትን ጥበባዊ ዘዴዎች ያስተምረዋል እንጂ በራሱ የቆመ ለየት ያለ ኢስላማዊ ጎዳና ወይም የሸሪኣ ዘርፍ አይደለም፡፡ ማንም ሰው የተሰውፍ ዘዴዎችን ሳይማር ኢባዳውን ማድረግ ይችላል፡፡ “ልቤ በትእቢትና በኩራት ተወጥራለችና ምን ይበጀኛል?” ብሎ የሚጨነቅ ከሆነ መድሃኒቱን ከተሰውፍ መንገድ መፈለግ ይፈቀድለታል፡፡ እዚህ ላይ የታዋቂውን የሱፊ ጥበብ አዋቂ የሼኽ አብዱልቃዲር አል-ጄይላኒን ምሳሌዎች ልጥቀስ፡፡ ሼይኽ አል-ጄይላኒ “አል-ጉንያ ሊጣሊብ ጠሪቀል ሀቅ” በተባለ መጽሀፋቸው ውስጥ እንዲህ ይላሉ፡፡ መቼም ቢሆን አትማል፤ መማል ካስፈገለ ግን በአላህ ስም ብቻ ማል! በምላስህ አትዋሽ! ጥሩ ነገር ብቻ ተናገር! በመንገድህ ላይ በእድሜው ካንተ የሚያንስ ሰው ቢያጋጥምህ “ከርሱ የተሻልኩ” ነኝ ብለህ አታስብ፡፡ ከዚህ ይልቅ በልብህ “ይህ ልጅ በምድር ላይ የኖረበት ዘመን ከኔ እድሜ ያንሳል፡፡ ስለዚህ ሀጢአቱም ከኔ ያነሰ ነው” በል፡፡ በእድሜው ካንተ የሚበልጥ ሰው ከገጠመህ ደግሞ “ይህ ሰው በዚህች ምድር ላይ ከኔ እድሜ ለሚበልጥ ጊዜ ኖሯል፤ ስለዚህ ለአላህ ባደረገው ኢባዳ ከኔ ይበልጣል” በል እንጂ በመጥፎ ነገር አትጠርጥረወ፡፡ ደስ ይላል አይደል? ከማስደሰቱ ጋር መጠየቅ ያለበት ጥያቄ “ሼኽ አብዱልቃዲር የተናገሯቸው ነገሮች ከኢስላማዊው ሸሪዓ ጋር ይቃረናሉ ወይ?” የሚለው ነው፡፡ ሼኽ አብዱልቃዲር የጻፉት ነገር ከኢስላማዊ ሸሪዓ ውጪ አይደለም፡፡ ይልቅ ኢስላማዊ ሸሪዓን በትክክል ለመተግበር ያግዛል፡፡ ተሰውፍ ማለትም እንዲህ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ነው ሙስሊሞች ልባቸውን ከበሽታ የሚፈውሱባቸውን ልዩ ልዩ ምክሮች የሚሰጡ መጽሀፍት መጻፍ የተጀመሩት፡፡ አንዳንድ መምህራንም ሙሉ ጊዜያቸውን ለዚሁ ሰጥተው የማስተማሪያ ማእከላትን ያቋቋሙት ለዚሁ አላማ ነው፡፡ ተሰውፍ ሲበላሽ ጥንት በሰላማዊ ሁኔታ የተጀመረው ተሰውፍ ከዘመናት በኋላ መስመሩን ሳተ፡፡ ሰዎችን በሸሪአ ላይ የሚያበረታታ መሆኑ ቀርቶ ከሸሪአ የሚያስወጣ መሆን ጀመረ፡፡ ለምሳሌ፤ በተሰውፍ ስም ከሸሪአ ጋር የሚቃረኑ ተግባራትን መፈጸም ተጀመረ፤ ዳንስና ሙዚቃ እንኳ በተሰውፍ ስም ተፈቀዱ (ለምሳሌ በቱርክ ያሉትና “Whirling Dervishes” የሚባሉት የመውላዊ ጠሪቃ ተከታዮች የሚያደርጉትን የዳንስ ትርኢት “ዚክር” ነው ይሉታል፡፡ አስተግፊሩላህ!!) እንደ አል-ሀለጅ እና ኢብን አረቢ የመሳሰሉት “ሱፊ” ነን ባዮች ደግሞ ግልጽ የወጣ ኩፍር ውስጥ የሚያስገቡ ፍልስፍናዎችን በተሰውፍ ስም መጻፍና ማስተማር ጀመሩ፡፡ ለምሳሌ አለ-ሀለጅ “ማነው ሀቅ?” በሚል ጥያቄ ጀመረና “አነል ሀቅ”፤ ማለትም “አል-ሀቅ እኔ ነኝ” የሚል ፍልስፍና ላይ ደረሰ፡፡ እኛ ሙስሊሞች “አል-ሀቅ” የምንለው አላህን ብቻ ነው፡፡ ሰውዬው ግን ራሱን “አል-ሀቅ” ብሎ ጠራ፡፡ ይህንን እንዲተው ቢመከር እንቢ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ በጊዜው የነበረው የባግዳድ ኸሊፋ በስቅላት ቀጣው፡፡ ከአይሁድና ክርስቲያን መነኮሳት ጋር የተቀራረቡ ሙስሊሞች በበኩላቸው በተሰውፍ ስም ምንኩስናን ወደ ኢስላም አስገቡ፡፡ አንዳንዶቹ ተሰውፍን ከልብ ንጽህና አርቀው ከአላህ ጋር በቀጥታ የምንነጋገርበት ጥበብ ነው እያሉ ከሸሪዓው ያነፈገጡ የግጥም ውዳሴዎችን የሚያቀርቡበት መድረክ አደረጉት፡፡ አንዳንዶቹ ከዚህም ራቅ ብለው ተሰውፍን ከአላህ በስተቀር ማንም ሊደርስበት የማይችለውን ስውር አለም (ገይብ) የሚመረምሩበት መነጽር አደረጉት፡፡ ተሰውፍ ኢስላማዊ ባህልን መከተል ሲገባው የባእዳን ባህል ተከታይ የሆነበት ሁኔታም ተፈጠረ፡፡ ከ16ኛው ክፍለ ዘመን ወዲህ ነገሩ ሁሉ ተቀየረና “ተሰውፍ” የአውሊያ መቃብሮች የሚመለኩበት የሽርክ ጋሻና መከታ ሆነ፡፡ ተሰውፍ በስተመጨረሻው ላይ እንደዚህ ውጥንቅጡ የወጣ ዝባዝንኬ ነገር ሆነ፡፡ ለዚህ ሁሉ ምክንያት የሆነው “ጠሪቃ” እና “ሀድራ” የሚባሉ ነገሮች መከሰታቸው ነው፡፡ “ጠሪቃ” የተሰውፍ ዚክር ከአንዱ ሼኽ ወደሚቀጥለው ሼኽ የሚተላለፍበት መንገድ ነው፡፡ በጠሪቃው ውስጥ የሚታቀፉት ሼኾች እንደ ተማሪና መምህር ሳይሆን እንደ ጌታና ባሪያ ነው የሚተያዩት፡፡ ሀድራ ደግሞ አንድ ሼኽ ዚክርን የሚያስተምርበት ማእከል ማለት ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን ሼኹ ራሱ የሚመለክበት ማእከል ሆኖ ተገኝ፡፡ ከዚህ ሌላ የሀድራ ሼኾች ራሳቸውን ወደ ፈውዳላዊ ባላባቶች እየቀየሩ ሀብት ያግበሰብሱ ገቡ፡፡ እነዚህን አላማዎች የሚደግፉላቸውን የቅጥፈት ወሬዎች፤ ተረቶች፤ ታሪኮች ወዘተ ማስወራት ጀመሩ፡፡ አላህ በቁርአኑ የተናገረው “የአላህ አውሊያ” የሚለው አባባል ትልቅ የማጭበርበሪያ ዘዴ ሆነ፡፡ በዚህ ውጥንቅጡ የወጣ ሁኔታ ውስጥ ነው በርካታ የተቃውሞ ድምጾች በተሰውፍ ላይ የተነሱት፡፡ ከነዚህ ድምጾች መካከል በጣም ከፍ ብሎ የተሰማው የሼይኹል ኢስላም ኢብን ተይሚያህ ድምጽ ነው፡፡ ሼይኹል ኢስላም ኢብን ተይሚያ በተሰውፍ ስም የሚነገድበትን አይን ያወጣ ኩፍር፤ ሽርክ፤ ቢድአና ባእድ አምልኮ በሀይለኛ ሁኔታ ተቃውሟል፡፡ ነገር ግን ኢብን ተይሚያህ አሁን እንደሚባለው ተሰውፍን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አላደረገውም፡፡ ሙስሊሞች በዚክር ከልብ በሽታ የሚፈወሱበትን “ተሰውፍ” በእጅጉ ደግፏል፡፡ ኢብን ተይሚያህ እነ ሼይኽ አብዱልቃዲር አል-ጀይላኒ ያስተማሩትን እውነተኛ ተሰውፍ በጣም ያበረታታ ነበር፡፡ እርሱ የተቃወመው በተሰውፍ ስም የሚካሄዱትን ከላይ የገለጽኳቸውን አስነዋሪ የሆኑ ኢ-ኢስላማዊ ድርጊቶችና አመለካከቶችን ነው፡፡ አህባሾችና የተሰውፍ አመለካከታቸው ከላይ የቀረበውን ትንተና ያነበበ ሰው አህባሾች በተሰውፍ ላይ ያላቸውን አመለካከት በቀላሉ ይረዳል ብዬ አምናለው፡፡ ስለዚህ ነገሩን በዚሁ እናሳጥረው፡፡ ለመሰናበቻ አንድ ምሳሌ ልስጣችሁ፡፡ በተለምዶ “ገሪባ” ሲባል ሰምታችኋል? ምን ማለት ነው? አህባሾች “ሱፊ” የሚሉት ልቡን ከበሽታ ለማንጻት የሚታገለውን እውነተኛ ሱፊ ሳይሆን ነፍሱን ለሼይኽና ለአውሊያ አምልኮ የሰጠውን እንደ “ገሪባ” አይነት ሰው ነው፡፡ የአውሊያ መቃብሮችን በየጊዜው እንድንዘይርና እንድንስም ለማድረግ ሲባል አህባሾች እንደ ምክንያት ከሚያቀርቡልን ሰበቦች አንዱ “ተሰውፍ” ነው፡፡ ነኡዙ ቢላህ!! በተሰውፍ ስም ግልጽ ሽርክ?? አላህ ከሽርክ ይጠብቀን!! በተሰውፍ ስም ሽርክን ከሚያበረታቱ አሳሳቾችም ይጠብቀን!! አሚን!!!

Related Articles

Latest Articles

Most Popular