Media hula ye ethiopia muslim lay tenesa ende ? ሪፖርተሮች>>መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ተገዷል ale

የሙስሊሙ ማኅበረሰብን የሚያወዛግበው አክራሪነት ጣልቃ ገብነት ወይስ አስተምህሮ? SUNDAY, 18 MARCH 2012 00:00 BY HENOCK YARED , YEMANE NAGISH & SOLOMON GOSHU HITS: 853 View Comments ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በእስልምና ሃይማኖት ሥር ያሉ በዋህቢያንና በአሕባሽ አስተምህሮ የአካሄድ ልዩነታቸውን ቢያሳዩም፣ ልዩነቱ እየተካረረ በመሄዱ መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ተገዷል፡፡ የቡድኖቹ መሠረታዊ ልዩነት ከዋነኛዎቹ የእስልምና አስተምህሮቶች (መዝሃብ) የተነሳ ቢሆንም፣ አንዱ አክራሪ ሌላው ለዘብተኛ ተደርጎ እየተወሰደ ይገኛል፡፡ ቡድኖቹ በቁርአን፣ በሃዲስ (በነብዩ መሐመድ አስተምህሮት) ላይ ልዩነት የሌላቸው ሲሆን፣ በአተረጓጎምና በአስተያይ (ቂያስና ቂጅማ) ላይ እንደሚለያዩ ይነገራል፡፡ ከ7ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ አንድ ሃይማኖት ከፖለቲካ፣ ከማንነትና ከባህል ጋር ቁርኝነት ያለው ቡድን ሆኖ ቢቆይም በቅርብ ዓመታት ከውጭ ሲታይ ሃይማኖታዊ የሚመስል ውስጡ ግን ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ልዩነት በሁለቱ ቡድኖች መካከል ተፈጥሯል፡፡ ይህ ልዩነት ዓለም አቀፋዊ እንጂ አገር በቀል እንዳልሆነም ባለሙያዎች እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ ሪፖርተር ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ የታሪክ፣ የፖለቲካና የሕግ መነሻዎችን በማንሳት የሁለቱን ቡድኖች አለመግባባት ከራሳቸው አንደበትና የመንግሥትን ጣልቃ የመግባት ምክንያት ከመንግሥት አንደበት አንባቢው እንዲረዳ በሚከተለው መንገድ አቅርቦታል፡፡ በዓለም ታሪክ የመንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት የእርስ በርስ ግንኙነት ጠንካራ በመሆን ለሺሕ ዓመታት ቆይቷል፡፡ በዚህም በአብዛኛው የመንግሥት ቢሮክራሲ አመራር በሃይማኖት ተቋማት የሚፀድቅበት ሁኔታ (The Divine Power Theory) ነበር፡፡ ሆኖም በዚህ የእርስ በርስ ግንኙነት በአንዱ ወቅት የመንግሥት ቢሮክራሲው በሌላ ወቅት የሃይማኖት ተቋማቱ የበላይነት የሚይዙበት ሁኔታ ነበር፡፡ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተቀጣጠለው የህዳሴ ንቅናቄ ለመጀመሪያ ጊዜ የሃይማኖት ተቋማት ከመንግሥት ተለይተው መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ጠቁሞ ነበር፡፡ ይህም ሃይማኖት መንግሥት በሳይንስ፣ በትምህርትና በዲሞክራሲ ጽንሰ ሐሳቦች ላይ ትኩረት እንዳይሰጥ ይከላከላል ከሚል መነሻ ሐሳብ የተሰጠ ነበር፡፡ ነገር ግን ሃይማኖትና መንግሥት ተነጣጥለው መሥራት አለባቸው የሚለው ጽንሰ ሐሳብ ተቀባይነት ለማግኘትና የሕግ መሠረት ለመያዝ ተጨማሪ መቶ ዓመታትን ጠይቋል፡፡ የሁለተኛው የዓለም ጦርነትን መጠናቀቅ ተከትሎ ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን ተቀባይነት ባላቸው መርሆዎች ለመምራት የተረቀቀውና እ.ኤ.አ. በ1945 ሥራ ላይ የዋለው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር በአንቀጽ 1 ላይ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ ልዩነት/አድልኦ በዜጎች ላይ ሊፈጸም እንደማይገባ ያትታል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1948 የተረቀቀው ሁሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀጽ 18 ላይ የዜጎች የሃይማኖት መብት የማመንን ብቻ ሳይሆን እምነትን የመቀየር፣ ሃይማኖትን የማስተማር፣ ተግባራዊ የማድረግ፣ የማምለክና የመከተል ነፃነትን ጭምር እንደሚያጎናጽፍ አረጋግጧል፡፡ የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ ቃል ኪዳን በአንቀጽ 18(3) ላይ መንግሥታት የሃይማኖት ወይም የእምነት ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ከሕዝብ ደህንነት፣ ሰላም፣ ጤናና ሞራል አንጻር እንዲሁም የሌሎች ዜጎችን መሠረታዊ መብቶች ለመጠበቅ ገደብ ሊጥሉ እንደሚችሉና በእነዚህ ሁኔታዎች የመንግሥታቱ ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት እንዳለው ይደነግጋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ1981 የተረቀቀው ሃይማኖትና እምነትን መሠረት ያደረጉ ሁሉንም ዓይነት ያለመቻቻልና አድልኦ የማስወገድ የተባበሩት መንግሥታት ድንጋጌ በአንቀጽ 6 ላይ ዜጎች እንደ ግለሰብ የማመን፣ የማምለክና የመሰባሰብ መብት ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታቸውን ወይም እምነታቸውን በቡድን የማስተማርና መሪዎቻቸውን የማሰልጠንና የመመደብ፣ በሃይማኖት ጉዳይ ከሌሎች ቡድኖች ጋር ግንኙነት የመፍጠር መብት እንዳላቸው ይገልጻል፡፡ በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ሁኔታ የሃይማኖት ወይም የእምነት መብት የማመን፣ ያለማመንና እምነትን የመቀየር መብት (The right to believe, unbelieve and disbelieve) የተረጋገጠ ሲሆን፣ ይህ የመብት ጥበቃ በመንግሥትና በሃይማኖት ተቋማት ተለያይቶ መሥራት ላይ (Secularism) የተመሠረተ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከላይ የገለጽናቸው ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ፈራሚ አገር ነች፡፡ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በአንደኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ የገባው የክርስትና እምነት ከአራተኛው ክፍለ ዘመን እስከ 1967 ዓ.ም. ድረስ የመንግሥት ሃይማኖት በመሆኑ አገሪቱ ለሌሎች እምነቶች የምትመች እንዳልነበረች የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡ ደርግ በሕግ የሃይማኖቶችን እኩልነት ቢያረጋግጥም፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በተመሠረተበት ጊዜ በመንግሥት ምክር ቤት ሥር የሃይማኖት ጉዳዮች ሚኒስቴር አቋቁሞ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በተግባር ያን ያህልም ለውጥ እንዳልመጣም ይነገራል፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከያዘ በኋላ ዜጎች ማንኛውንም እምነት የመከተል መብት እንዳላቸው፣ ሁሉም ሃይማኖቶች እኩል መሆናቸውንና ሃይማኖትና መንግሥት የተለያዩ መሆናቸውን በሕግም በተግባርም አረጋግጧል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ከለላም ያለው መብት ሆኗል፡፡ በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሥርም የሃይማኖቶች ጉዳይ ዳይሬክቶሬት አቋቁቋማል፡፡ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ለምን? የሃይማኖት ተቋማት የኅብረተሰቡን ሞራል፣ ሥነ ምግባርና መልካም እሴቶችን በማዳበር በጎ ተፅዕኖ በመፍጠር የመንግሥት አጋር መሆን ብቻ ሳይሆን የግለሰቦችን ነፃነትና ሰብዓዊ መብት በመግፈፍ በግለሰብና በማኅበረሰቡ ብሎም በመንግሥት ላይ አደጋ የመፍጠር አቅምና ጉልበቱ አላቸው፡፡ በዚህ ጊዜ የሚነሳው ትልቁ ጥያቄ የሃይማኖት ተቋማቱ መሪዎች በግለሰብ ደረጃ ወይም ደግሞ ተቋማቱ ይፋዊ በሆነ መንገድ በሃይማኖት ምክንያት የአገሪቱን ሕግ ከተላለፉ ከሕግ የበላይነት ሊያመልጡ ይችላሉ ወይ የሚል ነው፡፡ ሃይማኖቶች እርስ በርስና በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የታቀፉ ቡድኖች ግጭት የተለመዱ ቢሆንም፣ ከሃይማኖት ቡድኑ ውጪ አገርን፣ ሰብዓዊ መብትን፣ የግለሰብና የቡድን መብትን፣ ብሔራዊና ዓለም አቀፋዊ ደኅንነትን የመንካት አቅሙ ሰፊ ነው፡፡ በተለይ ሃይማኖታዊ አክራሪነት የሃይማኖት መብት አካል የሆነውን ያለማመንና ትችት የመሰንዘር ብሎም ከነበረበት የሃይማኖት እምነት ወይም ቡድን የተለየ ግለሰብና ቡድን ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችና ጭቆናዎች ባለፉት 20 ዓመታት እየጨመረ በመምጣት የዓለም ስጋት እስከመሆን ደርሷል፡፡ ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተለያዩ ሃይማኖቶች እርስ በርስና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፣ በፕሮቴስታንት ቤተ ክርስቲያኖችና አሁን በቅርቡ ደግሞ በእስልምና እምነት ሥር ያሉት የዋህቢያና የአሕባሽ ቡድኖች ግጭትን ለማብረድ የኢፌዴሪ የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ለመግባት ተገዷል፡፡ ለመሆኑ የመንግሥት ጣልቃ መግባት ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ተቀባይነትስ አላቸው? 1. ብሔራዊ ደኅንነት ከላይ እንደተገለጸው መንግሥት የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የሃይማኖት ጉዳይ ላይ ጣልቃ ሊገባ ይችላል፡፡ በእርግጥ በአንድ ሃይማኖት ውስጥ የተነሳው የሐሳብ ልዩነት የመንግሥትንና የሕዝብን ሰላምን ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሏል ለማለት የሚቻለው መቼ ነው? ለሚለው ጥያቄ ግልጽ የሆነ ምላሽ የለም፡፡ ቢሆንም የግልጽና ተጨባጭ አደጋ መለኪያ (Clear and Imminent Danger Test) ወይም የአደገኛ አዝማሚያ መለኪያ (Dangerous Tendency Test) እንደ ሁኔታው ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፡፡ በአንድ ሃይማኖት ውስጥም ሆነ በተለያዩ ሃይማኖቶች መካከል ባሉ የሃይማኖቱ መሠረታዊ ሁኔታዎች ዙሪያ ያሉ አለመግባባቶች ላይ ሐሳብን በነፃነት መግለጽና መደራጀት ብሎም በአስተምህሮቶቹ ዙሪያ ደጋፊ የማሰባሰብ የውትወታ ሥራ (Advocacy) የሃይማኖት መብት አካል ቢሆንም፣ ነፃ የሐሳብ ልውውጡ የአገርን ሰላምና ደኅንነት አደጋ ላይ ወደሚጥል ተግባር የሚቀየር ከሆነ (Adversive Advocacy) የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተቀባይነት ይኖረዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከሰሞኑ በሁለት የተለያዩ የእስልምና ቡድኖች መካከል ያደረገው ጣልቃ ገብነት ከደኅንነትና ሰላም ጋር ብሎም ከሽብርተኝነት ጋር የተገናኘ ማስረጃ አግኝቻለሁ ማለቱ የግልጽና ተጨባጭ አደጋ መለኪያን መጠቀሙንና የሐሳብ ልዩነቱ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚለውጥ መሆኑን በተጨባጭ ማረጋገጡን በመግለጽ ጣልቃ ገብነቱ ተቀባይነት እንዳለው እየገለጸ ነው፡፡ 2. የግለሰቦች መብት ጥበቃ ዜጎች የመረጡትን እምነት የመከተል መብት ያላቸው ከሆነ ይህ መብት በእምነቱ ላይ ያላቸውን የሐሳብ ልዩነት የማራመድ መብትንና ጭራሹን ያለማመን መብትን ይጨምራል፡፡ አሁን በሁለቱ የእስልምና ቡድኖች መካከል የሐሳብ ልዩነቱን የሚያራምዱት ቡድኖች አንዱ አንዱን ‹‹እስላም አይደለም›› እስከ ማለት መድረሳቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪዎች፣ የመንግሥት ጣልቃ ገብነት የአገሪቱን ሰላም ከማስከበር ዘሎ ለእምነቱ ተከታይ ግለሰቦች የሕግ ከለላ በመስጠት መብታቸውን ሊያስከብር እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በዚህም የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ተቀባይ የሚሆንበት ተጨማሪ ምክንያት ይጠቁማሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት መጅሊስ የአሕባሽ ትምህርትን አምጥቶ ሥልጠና እንዲሰጥ የተገደደበት ምክንያት የዋህቢያ ፀረ ዜጎች እምነትና እስላማዊ መንግሥት ለመመሥረት ይንቀሳቀስ በሚል ነው፡፡ አቶ መረሳ ረዳ በፌዴራላዊ ጉዳዮች ሚኒስቴር የሃይማኖትና የእምነት ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ጄነራል በጉዳዩ ላይ ያስጠኑት ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የዋህቢያ አስተምህሮ በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች ለተከሰቱ ሃይማኖታዊ ግጭቶች መሠረት መሆኑን ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱንም የሚጥስ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ከመጅሊስ ጋር በመተባበር የአሕባሽ ትምህርት እየሰጠ ያለው፣ በአመለካከት ደረጃ የሙስሊሙን ኅብረተሰብ ንቃት ህሊና ከፍ ለማድረግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ሰሞኑን በወቅታዊ ጉዳዮች መግለጫ የሰጡት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሬድዋን ሁሴን ይህንን አስመልክተው፣ ‹‹ችግሩ ሃይማኖታዊ አይደለም›› ያሉበትን እንዲህ በማለት አስረድቷል፡፡ ‹‹በሸሪዓ ሕግ ነው የምተዳደረው ብለህ ከተነሳህ፣ ሽፋኑ ሃይማኖታዊ ነው፡፡ ይዘቱ ግን ሃይማኖት አይደለም፣ ፖለቲካ ነው፡፡ የሸሪዓ መንግሥት መመሥረት ፖለቲካ እንጂ ሃይማኖት አይደለም፡፡ እስልምና በሸሪዓ ካልታገዝክ አይልም፡፡ በሸሪዓ የመተዳደር አጀንዳ የሥልጣን ፍላጎት እንጂ የእስልምና ግዴታ አይደለም፡፡ የሥልጣን ጥያቄ ነው፤›› ብለዋል፡፡ በሌሎች ሃይማኖቶችም በተለይ በኦርቶዶክስ ‹አንድ አገር፣ አንድ ሃይማኖት› የሚለው አስተሳሰብ በመጥቀስ፣ ‹‹ሽፋኑ ከእምነቱ ጋር ዝምድና የለውም፤›› ይላሉ፡፡ መንግሥት ዋህቢያ የሚባለውን እንቅስቃሴ እስላማዊ መንግሥትን መመሥረትን ጨምሮ የዜጎች ሕገ መንግሥታዊ የእምነት ነፃነት በመጣስ የራሱን ብቻ እንዲከተሉ የሚያስገደድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ትምህርቱ ከሳዑዲ ዓረቢያ የመጣ ሲሆን፣ ሃይማኖትና ሥልጣን በጋራ ተደጋግፈውና ተስማምተው አንዱ ሌላውን ተሸክሞ የሚኖርበት መሆኑን ይገልጻል፡፡ የዋህቢያ ትምህርት፣ ባህላዊ የእስልምና እምነትን አስቀርቶ በቅዱስ ቁርአንና በኻዲስ ትምህርት የሚያምኑ አስተምህሮ መሆኑን የሚገልጹ ደጋፊዎቹ ደግሞ፣ የአሕባሽን ትምህርት ቅዱስ ቁርአን መሠረታዊ ማዕዘኖችን ይጥሳል በሚል ይቃወማሉ፡፡ መንግሥት፣ ከመጅሊስ ጋር በመሆን የአሕባሽ ሥልጠና ትምህርት መስጠቱ መፍትሔ እንደማይሆን ይገልጻሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት ‹‹እስልምና ጉዳዮች›› እና ‹‹ሰላፍያ›› የመሳሰሉ ሚዲያዎች የመንግሥትን ጣልቃ ገብነት አክርረው የሚቃወሙ ሲሆን፣ መንግሥት ከእምነት እጁን እንዲያወጣ ይጠይቃሉ፡፡ አቶ አደም ካሚል የተባሉት በሳዑዲ ዓረቢያ ላለፉት 30 ዓመታት የኖሩ ኢትዮጵያዊ ተመራማሪ፣ በመንግሥት እየተፈጠረ ያለው ጥርጣሬና ችግር መነሻ የመጅሊስ ድክመት መሆኑን ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ መንግሥት ከሚለው በተቃራኒ የአሕባሽ ትምህርት መሠረታዊ የእስልምና እምነት የሚጻረር መሆኑን ነው፡፡ መፍትሔውም፣ መጅሊስ (እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት) ማጠናከርና በተማረ የሰው ኃይል እንዲሠራ ማድረግ ነው፡፡ እንደ እሳቸው እምነት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ እስልምና መሠረት ያለውና የራሱ የፀና ትምህርት ስላለው በማናቸውም መጤ እምነቶች አይጠቃም፡፡ ዋህቢያ የሚባለው እምነት የለም የሚሉት እኚሁ ምሁር፣ አይዲዮሎጂው ግን ምንም ክፋት እንደሌለው ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት አሕባሽ የተባለው አስተምህሮ ማምጣቱን በመቃወም፡፡ በአሁኑ ወቅት፣ በአወሊያ ትምህርት ማዕከል የተከሰተው ውዝግብ የዚሁ አካል ሲሆን፣ መንግሥት አንዳንድ ለውጦች ለማድረግና ሥርዓተ ትምህርቱን ለማድረግ የተንቀሳቀሰው የዋህቢያ ማፍለቂያ ቦታ ሆኗል በሚል ነው፡፡ የመንግሥትንና ሕገ መንግሥታዊ የዜጎች መብት የሚጥስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን በምክንያትነት እየጠቀሰ ሲሆን፣ መንግሥትን የሚቃወሙ በበኩላቸው በጣልቃ ገብነት እየወነጀሉ ነው፡፡ የአወሊያው ውዝግብ የሕዝበ ሙስሊሙን ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ለማፈላለግ የተወከልኩ ኮሚቴ ነኝ፤ በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች በሚገኙ ሙስሊሞች በተፈረመ ፒቲሺን ውክልና አለኝ፤ የሚለው ኮሚቴ በአወሊያ በየሳምንቱ ዓርብ መሰባሰብ ከጀመረ 10ኛ ሳምንቱን እንደያዘ ይናገራል፡፡ የኮሚቴው ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አሕመድ መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥያቄዎቻቸው የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ የአወሊያ ትምህርት ቤት በቦርድ ስለመመራትና የአሕባሽ አስተምህሮን በተመለከተ ነው፡፡ ‹‹አመራሮቹ የመጡት በ2001 ዓ.ም. ላይ ነው፡፡ የቀድሞዎቹ ሲታገዱ ባለአደራ ሆነው የመጡ እንጂ ውክልና ተሰጥቷቸው የመጡ አይደሉም፡፡ ዛሬ ነገ ምርጫ ይካሄዳል ቢባልም አልተካሔደም፤ የመጀመሪያው ጥያቄ ሕዝበ ሙስሊሙ የመረጣቸው መሪዎች ሊቀመጡ ይገባል የሚል ነው፡፡›› የአሕባሽ አስተምህሮን በተመለከተም፣ ‹‹አስተምህሮው ከእስልምና መሠረታዊ አስተምህሮ ወጣ ያለ ነው ብለን ነው የምናምነው፡፡ አስተምህሮው በራሱ በግሉ በአገሪቱ ውስጥ ሊንቀሳቀስና ተቋም መሥርቶ ሊያስተምር ይችላል፤›› ያሉት ኡስታዝ አቡበከር፣ አሕባሽ ሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል የማይቀበለው አስተሳሰብ ነውና በሙስሊሙ ማኅበረሰብ ተቋም በሆነው መጅሊስ ከለላና መሪነት ይባስ ብሎ የማስገደድ ተግባር እየተፈጸመ ያለው የተወሰነ ፍላጎት ባላቸው የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት አጋዥነት ሳይቀር በየመስጂዱ የሚሰጠው ትምህርት እንዲቆም እንፈልጋለን ብለዋል፡፡ አወልያ ተቋምን በተመለከተም አወልያ በሕዝብ ለረዥም ጊዜ ሲመራ ቆይቷል፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መጅሊስ (እስልምና ጉዳይ) ተረክቦታል፡፡ ከተረከበው በኋላ ተቋሙን የማሳደግ ተግባር አልፈጸመም፡፡ ተቋሙን የበለጠ ከማሻሻል ያሉበትን ችግሮች ከመቅረፍ ይልቅ አሠራሩን የመቀየርና ይባስ ብሎ የማዳከም ሁኔታ ታይቶበታል ያሉት ገጽታውን በማመልከት ነው፡፡ ‹‹አወሊያ የሙስሊሙ ብቸኛና ትልቁ ተቋም ነው፡፡ ቢያንስ በውስጡ መስጊድ፣ ኮሌጅ፣ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ሆስፒታል፣ የሕፃናት ማሳደጊያና ሁሉን ነገር የያዘ የተሟላ ተቋም ነው፡፡ ይህን የያዘ ተቋም አላግባብ ዕርምጃ ሲወሰድበት ሙስሊሙ ማየት ስለማይችል አገራዊ ጥያቄ ሆኖ መጥቷል፡፡›› የካቲት 26 ቀን 2004 ዓ.ም. በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ስድስት ሰዓት የፈጀ ውይይት መደረጉን ያስታወሱት ኡስታዝ አቡበከር፣ በመድረኩ የተሰጠው ምላሽ የሚመስል ግን ማብራርያ የሚፈልግ ብዥታ እንዳለው የመጅሊስ ምርጫ ይካሄዳል ቢሉም መቼ እንዴት፣ በምን መልኩ ይካሄዳል? የሚያስመርጠውንስ ገለልተኛ ማን ይመርጠዋል ቢባል ምላሽ ያልተገኘበት በማለት ገልጸዋል፡፡ አወሊያን በተመለከተም ሕዝበ ሙስሊሙ የሚወክላቸው ሰዎችና ምሁራን በቦርድ እንዲመሩት ቢጠየቅም፣ ቦርዱን ማን ያስመርጣል? በሚለውም ስምምነት ላይ እንዳልደረሱና ድጋሚ ለውይይት ይጠራሉ ብንልም አልጠሩንም ብለዋል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም የውይይት መድረክ እንዲዘጋጅልንም ጠይቀን ምላሽ እየጠበቁ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በወቅቱ በተፈጠረው ሁኔታ ስለዋህቢያም ይነሳል ብለን ለጠየቅነውም ሰብሳቢው ሲመልሱ፣ ‹‹ዋህቢያ ስል ተቋማዊ ሆኖ ባለቤት ይዞ የመጣ አካል ካለ ያ አካል ነው ባለቤት ሆኖ የሚቀርበው፤ ነኝ የሚል አካል ካለ ዋህቢያ ነኝ ብሎ ስለሚያምንበት ሴክት መግለጽና ማስረዳት ግድ ይለዋል፣ ይገባዋል ብለን ነው የምናምነው፡፡ እዚህ ባለው ግን በአሕባሽና በመጅሊስ ላይ ባለው ሒደት ውስጥ ዋህቢያ የሚል ነገር የለም፣ ከሙስሊም ማኅበረሰብ ጋር እየተካሄደ ያለ ተቋምን ወይም መሠረታዊ እምነትን በተመለከተ እየተደረገ ያለ ፍጥጫ እንጂ ከሌላ ሴክት (የእምነት ክፍል) ጋር የተያያዘ አይደለም፤›› በማለት ተናግረዋል፡፡ በወቅታዊ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳይ ላይ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ኡላማዎች ምክር ቤት አሕባሽ የሚባል ዲን (አስተምህሮ) እንደሌለ አስረግጦ ተናግሯል፡፡ ‹‹አሕባሽ የሚባል ዲን በኢትዮጵያም ሆነ ከኢትዮጵያ ውጭ በማንኛውም ዓለም የለም፡፡ አሕባሽ ማለት ኢትዮጵያውያን ከሚል የመጣ ነው፡፡ የኢትዮጵያዊ ሼኽ የሚከተሉ ወይም እርሱ ያስተማራቸው በሚል አሕባሽ መጣ እንጂ ዲን ማለት አይደለም፤›› በማለት አብራርቷል፡፡ ምክር ቤቱ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በአዲስ አበባ ከተማና በተለያዩ ክልሎች እየተሰጠ ያለው ሥልጠናም የሙስሊሙን የዲን ዕውቀት ለማጐልበት ታስቦ ትክክለኛውን መንገድ እንዲይዙ ለማድረግ የተከናወነ እንጂ፤ አንዳንድ ወገኖች እንደሚሉት ሌላ እምነት ለመስበክ አይደለም፡፡ በምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ ሼክ ኢዘዲን አብዱል አዚዝ አገላለጽ፣ በትምህርት ሒደቱ ላይ በጠቅላላው ማስረጃ ተደርገው የተጠቀሱት ከቅዱስ ቁርአን ከኻዲስ፣ ከኢጅማዕና ከአራቱ መዛሂብ መሪዎች ሲሆን፣ ሥልጠናው እየተሰጠ ያለውም በፈቃደኝነት ነው፡፡ የኡላማዎች ምክር ቤት በኡላማዎች የሚሰጠውን ትምህርት የተከታተለ መሆኑን የገለጹት የምክር ቤቱ ዋና ጸሐፊ እንዳሉት፣ ሥልጠናውን በአሁኑ ጊዜ መስጠት ያስፈለገበት ምክንያት ነብዩ መሐመድ እንደገለጹት አፍራሽ የሆኑ አስተሳሰቦች፣ ብቃትና ዕውቀት የሌላቸው፣ ያለፉትን ኡላማዎች የሚያጣጥሉ ሰዎች የሚመጡበት ወቅት በመሆኑ ነው፡፡ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ምርጫ እንዲካሔድ ምክር ቤቱ ጥር 9 ቀን 2004 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ መወሰኑንና ምርጫው በአገር አቀፍ ደረጃ የሚከናወን በመሆኑ የቅድመ ዝግጅት ሥራው እየተካሔደ መሆኑንና ኅብረተሰቡም ራሱን ማዘጋጀት እንዳለበት ያመለከተው የኡላማዎች ምክር ቤት፣ ለዚህ ምርጫ የሚመጡ ሰዎች ለሙስሊም ኅብረተሰብም ሆነ ለአገራችን የሚበጁ፣ ሙስሊም ኅብረተሰቡን ወዳልተፈለገ አቅጣጫ የማይወስዱ ሰዎች መሆን እንዳለባቸው ጥሪ አድርጓል፡፡ አወሊያ ትምህርት ቤት ግን እንደሌሎች ትምህርት ቤቶችና መስጂዶች ሁሉ በመጅሊስ መተዳደር ያለበት መሆኑን አስታውቋል፡፡ አያይዞም በአሁን ጊዜ ትምህርት ቤቱ መደበኛ ሥራውን እያከናወነ መሆኑን ተቋሙን ያስተዳድሩ የነበሩ ድርጅቶች የአገሩን ሕግ ተከትለው መሥራት ባለመፈለጋቸውና የሠራተኞችን ወጪ መሸፈን ባለመቻሉ የእስልምና ጠቅላይ ምክር ቤት በጀት መድቦ ሥራውን እንዲቀጥል ማድረጉን አብራርቷል፡፡ ትምህርት ቤቱ አፍራሽ ለሆኑ አስተሳሰቦች ሽፋን ሆኖ መቆየቱን የገለጸው የኡላማ ምክር ቤቱ መጋቢት 6 ቀን ባወጣው መግለጫ፣ ‹‹ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የሚነገረውንና የሚሠራውንም ነገር እያረጋገጠ መሄድ ይሻላል ነው የምንለው፤ ዝም ብሎ በተነሳው ወሬ ማጎብደድ አብሮ መጓዝ አይደለም፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ ወደ ግርግር የሚመሩ አንዳንድ ሰዎች አሉ፡፡ ወይ ለጥቅማቸው ሲሉ ወይ ደግሞ ከውጭ የሚያገኙትን ነገር ፍለጋ በሙስሊሙ ሽፋን የሚንቀሳቀሱ ስላሉ እነዚህን ለይቶ ማወቅ ያስፈልጋል፤›› በማለትም አሳስቧል፡፡ (ለዚህ ዘገባ ኃይሌ ሙሉ አስተዋጽኦ አድርጓል)
Be the first to comment

Latest Articles

Most Popular