secret of success part 1 የስኬት ሚስጥሮች(ክፍል አንድ)

የስኬት ሚስጥሮች(ክፍል አንድ)

ይህ “የስኬት ሚስጥሮች” በሚል ርዕስ በተከከታታይ ለማቅረብ የታቀደው ኮርስ አንብባችሁ እንደመረጃ ብቻ እንድትይዙት ሳይሆን በውስጣችሁ አብላልታችሁት ስኬታማ ለመሆን የሚያስችላችሁን መንገዶች እንድትይዙ ለማድረግ ነው
“ስኬት” በዚህ ሰዓት ከ 7 ቢሊዮን ነፍስ በላይ ስኬትን ይመኛሉ፤ከገቡበት ስቃይና መከራ ወጥተው ሀሴትና ደስታ የተሞላበት ኑሮ ይፈልጋሉ፤ ስኬት ጠንክሮ በመስራት ብቻ የሚገኝ መስሎቸው ብዙዎች ጧት ማታ ይለፋሉ፤ግን ስኬታማ አልሆኑም፤ ስኬት ብዙ ሰዎች የሚመኙት ትንሽ ሰዎች ብቻ ግን ያገኟት! 

የሚደርሱብንን ችግር እና መከራ “ማወቅ ብቻ” በትግስትና በጽናት እንደንታግል አያደርገንም፤ በትዕግስትና በጽናት ለመታገል መጀመሪያ ራሰን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤ለውጥ ለማምጣት መጀመሪያ ራሳህን መለወጥ አለብህ፤አንተነትህ ለትግል ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ ልትጠይቀው ፤ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖችህን አብጠርጥረህ ልታወጣ ይገባሀል ፤የምትታገለው ለምን እና ከማን ጋር እንደሆነ ማወቅ አለብህ፤ ከምንም በላይ “ትግል”፣ “ስኬት”፤”ለውጥ” የሚሉ ቃላቶችን ስትጠቀም መጀመሪያ ራስህን ማሸነፍ እንዳለብህ መዘንጋት የለብህም፤ ራስህን ሳታሸንፍ ሌላ ማንንም ማሸነፍ አትችልምና! በስራህ ስኬታማ በትግልህ ውጤታማ በንግድህ ትርፋማ ለመሆን ትፈልጋለህ፤ለዚህም ብዙ የስኬት ሚስጥሮችን እንዳሉ ብታውቅም ከየት መጀመር እንዳለብህ ግን አለወቅክ ይሆናል፡ለመሆኑ ስኬት ከየት ነው የሚጀምረው ?
የስኬት የመጀመሪያው ደረጃ ያንተው “ጠንካራ ዕምነት” ነው!
የሀይል፤ የቁርጠኝነትእና የመሰዋትንት መፍለቂያ “ፅኑ ዕምነት” ነው፡፡ ፅኑ ዕምነት ከሌለህ ትፍረከረካለህ፤ ትጠራጠራለህ፤ ትፈራለህ መጥፎ መጥፎ እንጅ ጥሩው አይታይህም፡፡ ፅኑ እምነት ስል እዚህ ላይ 6ቱን የኢማን መሰረቶች ልልህ ፈልጌ አይደልም (እነርሱ እንዳሉ ሁነው) 

በዚህ ንባብ “ጽኑ እምንት” 3 ነጥቦችን ያጠቃልላል፤

1. በራስህ መተማመን፤ “እችላለሁ ” “አሳካዋለሁ” ብለህ መነሳት
“አልችልም” ፤”አቅሙ የለኝም” ፤“ማይሆነ ነገር” ፤ እነዚህን የመሰሉ ቃላቶች አዕምሮህን ሞልተውት ከሆነ ካሁኑ አእምሮህን ልታክመው ይገባህል፤ ስኬታማ የሆኑ ሰዎች “ለስኬት የተመረጡ” ወይም የተለየ ብቃት እንዳላቸው አድርገህ አታስባቸው፤ እነሱም እንዳተው ተራ ሰው ነበሩ፤ ለስኬት የበቁት በውስጣቸው ያለውን ዕምቅ ሀይል መጠቀም ስለቻሉ ነው፤ “አልችልም” ሳይሆን “እችላለሁ ” ብለው ስለተነሱ ነው፤ እስቲ በራስህ ያለህን መተማመን ፈትሸው አንድ ስራ ብትጀምር አሳካዋለሁ የሚለውን የእምነትህን ጥንካሬ ለካው፤ “አልችልም ” “አይሳካልኝም” “አይሆንም” …..ለምን አትችልም?! ለምን አይሳካልህም? ! እንዴት አይሆንም?! እንደማትችል አይተሀዋል? ወይስ ገና ከጅምሩ “አልችልም” ብለህ ነው???….ይሄ ነው ያንተ ችግር!!!!
ገና ሳትጀምረው ልብህ ሞተ…..ታዲያ አንተ መብላት መጠጣት ብቻ ነው አንዴ የምትችለው….እነደዚህ ከሆነማ ከእንስሳ በምን ትለያለህ ፤ ከእንስሳ የተለየህበትን የማሰብ ችሎታ ካልተጠቀምክበት ምን ዋጋ አለው!!!

እስቲ አንድ ክስተት ላጫወትህ፤ አንድ መስሪያ ቤት አዲስ ሰራተኞችን ለመቅጠር ማስታወቂያ ያወጣል፤ የሚፈለጉት 3 ሰዎች ናቸው፤ አጠቃላይ ለውድድር የቀረቡት አራት ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ወዲያው ስራ አስኪያጁ መጥቶ ያለምንም ማወዳደሪያ መስፈርት 3ቱን ካሳለፈ በኋላ አንድኛውን አንተ “አትችልም” በማለት ይመልሰዋል፤ እሱም ግራ በመጋባት እንዴ !አትችልም ስትል አልገባኝም? ጥሩ ውጤት አለኝ እኮ! ደግሞ ሳታወዳድር እኮ ነው እነሱን ያሳለፍካቸው? ብሎ ማናጀሩን ይጥይቀዋል፤ ማናጀሩም ምንም መለስ ሳይሰጠው ወደ ክፍሉ ትቶት ገባ፤ ለውድድር ከቀረቡት ጓደኞቹ በምንም አያንስም በመልክ በቁመና በዕውቀት….ከእነሱ በምንም አያንስም ፤ ግን ማናጀሩ ያለምንም መስፈርት “አትችልም ” በማለት መልሶታል፤…….ማንበብህን አቁምና አንተ በሱ ቦታ ብትሆን ምን እንደሚሰማህ ግለጽልኝ፤ ለዚህ ማናጀር የሚኖርህንስ አለመካካት ንገረኝ(ከታች ኮሜንት ላይ ጻፍልኝ)…”አትችልም” ብሎኮ ነው የመለሰህ …ምናለ ዝም ብሎ 3 ሰዎች ነው የምንፈልገው ብሎ ቢመልስህ. ካሁን በኋላ ይሄንን ማናጀር ጠላት አድርገህ እንደምትይዘው እገምታለሁ፤ በዛች ቀን ከሱ በላይ ጠላት እንደሌለህ አድርገህም ልታስብ ትችላለህ…..ግን አትሸወድ!

“ላንተ ከራስህ በላይ ጠላት የለም!” ይሄ ስራ አስኪያጅ አንድ ስራ ነው” አትችልም” ብሎ ያባረረህ፤ በህይወት ዘመንህ የሆነ ስራ መስራት ካሰብክ በኋላ ገና ሳትጀምረው ፤ሳትሞክረው “አልችልም ” ብለህ ሳትሰራ የተውካቸው ስራዎቸን እስቲ ቁጠራቸው! ማናጀሩ ያለምንም መሰፈርት አትችልም ብሎ ቢያባርርህ ምን ይገርመሀል? አንተስ ያለምንም መስፈርት ዕድሜህን በሙሉ “አልችልም “እያልክ አይደል እንዴ ያሳለፍከው??? ታዲያ ምነው ማናጀሩ “አትችልም ”ሲልህ አበሳጨህ? ከሰዎች በአካል ብቃትም በዕውቀትም ሳታንስ ራስህን ለራስህ “አትችልም ” ስትለው ለምን የዚያ ግዜ አልተናደደክም? ታዲያ ከራሰህ በላይ ማን ጠላት አለ፤ አሏህ ጤንነትህን አሟልቶ ሰጥቶህ አልችልም ትላለህ….
ንቃ! “አልችል ማለትህን አቁም”፤ መስራት እንደምትችል “ማሰብና ማመን” የመጀመሪያ የስኬት ደረጃ ነው፤
መጅሊስ በእብሪተኝነት የአወሊያ መምህራኖችንና የመስጂዱን ኢማም ሢያባርር ማንም ምንም አያመጣም ብሎ ነበር ድርጊቱን የፈፀመው በእርግጥም በእኛ ውስጥም “መናደድና ተስፋ መቁረጥ” ይታይብን ነበር ሆኖም ግን ትግሉ ሲጀመር “እንችላለን” ብለን በመነሳታችን የተባረሩትን ብቻ ሳይሆን ማስመለስ የቻልነው ህዝቡ ውስጥ የነበረውን የፍርሃት ድባብ መግፈፍ ተችሏል ፤መጂሊስ አወሊያን የአህባሽ ማሠልጠኛ ማእከል ማድረግ ነበር የፈለገው ሆኖም ግን በአሁኑ ሰዓት አወሊያ የመጂሊስን መቃወሚያ የትግላችን ማዕከል ማድረግ ችለናል፡፡ 

2. የመጀመሪው” እምነት” መስራት እንደምትችል ማሰብ ነው ፤ ሁለተኛው እምነትህ ደግሞ የምትሰራው ስራ አዋጭ እና ትርፋማ እንደሚያደረግህ ፤ ትክክለኛ እና አግባብ ያለው ስራ እየሰራህ መሆኑን ማማን ነው፤ የምተስራው ስራ ትክክለኛ እና አትራፊ መሆኑን ካወቅክ ሙሉ ሀይልህን ትጠቀማልህ፤ ለምሳሌ ትምህርተ ስትማር ቤተሰብ ስላስገደደህ አይደልም መማር ያለብህ ፤ተምረህ የምታገኘውን ጥቅም በማሰብ መሆን አለበት፤ ቤተሰብ አስገድዶህ የምትማር ከሆነ ውስጥህ ያለውን አቅም አትጠቀምበትም ፤ ምክኒያቱም አላመንክበትማ! ንግድ ስትጀመር መሄጃ ስላጣህ ጊዜ ማሳለፊያ ብለህ መሆን የለበትም፤ እንዲህ በስራው ላይ ሳትተማመን የምትሰራቸው ስራዎች አይደለም ለስኬት ሊያደርሱ ለውድቀት እንዳይዳርጉህ መጠንቀቅ ይኖርበሀል፤ በአሏህ መንገድ ላይ ስትታገል ሰዎች ሲታገሉ አየሁ ብለህ መሆን የለበትም ! በአሏህ መንገድ ላይ መታገል ያለውን ጥቅም ካወቅክ በኋላ መሆን አለበት፤ ሳታምንበት ወይም ሳታስብበት በጀመርከው ስራ ላይ ችግር ቢያጋጥምህ ስራውን ጥለሀው ገሽሽ እንደምትል ግልጽ ነው፤ መማሩን ሳያምኑበት በቤተሰብ ግዳጅ ብቻ የሚማሩ ተማሪዎች ፤ እንደአጋጣሚ መምህሩ ቢቀር ምን ያህል እንደሚደሰቱ ሁላችንም እናውቃለን፤ ታዲያ እነዚህ ተማሪዎች ስኬታማ ይሆናሉ ብሎ ማሰብ ሞኝነት አይደለም? 
ስለዚህ ምንግዜም ቢሆን ስራ ከመጀመርህ በፊት በምትሰራው ስራ ልትተማመን ይገባሀል፤ 

3. ሶስተኛው ዕምነት፡ የጀመርከው ነገር በአሏህ ፈቃድ እንደሚሳካልህ ጽኑ እምንት ማሳደር አለብህ፤ ይሄ ስራ ይሳካልኛል አይሳካልኝም ብለህ ጥርጣሬ ውስጥ መግባት የለብህም፤ጥርጣሬ ወደ ኋላ እንጅ ወደፊት አይጎትትህም፤ የምትሰራው ስራ እንደሚሳካልህ ጽኑ እምነት ከሌለህ ያለህን ሙሉ ሀይል ለመጠቀም ትቸገራለህ፤ ሙሉ ሀይልህን መጠቀም እንድትችል በአሏህ ፈቃድ እንደሚሳካልህ እርግጠኛ መሆን ይገባሀል፤

በራስህ እና በምትሰራው ስራ “መተማመን ሲኖርህ” ያለ የሌለ ሀይልህን ተጠቅመህ ስራህን ለማሳካት ትጣጣራለህ፤ ወኔ እና መነሳሳት ይኖርሀል …ቁርጠኝነት እና ጥንካሬ ይኖርሀል፤ በትግልህ ላይ የሚገጥሙህን ችግሮች ለመጋፈጥ ቁርጠኝነት ይኖርሀል፤ እነ ቢላል፣ ዐማር፣ ያሲር፣ ሡመያ፣ (ረ.ዐ) ያን ያህል ሲሰቃዮ የቻሉት በውስጣቸው ባለው ጽኑ እምነት ነው፤ የሚያደርጉት ትግል እና የቆሙበት መንገድ ትክክለኛ መሆኑን በልባቸው ስለያዙ ነበር፤ በራሰህ እና በምትሰራው ስራ መተማማን ከሌለህ ትወላውላለህ ሀይልህ እንደ ሀሳብህ ይወላውላል ጥንካሬህ ይሟሽሻል፤ ወኔውም ተነሳሽነቱም አይኖርህም፤ስለዚህ ራስህን ለመቀየር ካሁኑ ጀምር ጊዜ አታጥፋ፤ እንደምትችል እንጅ እንዳማትችል ራስህን አታሳምነው፤ እንደምታሸንፍ እንደምትሽነፍ አታስብ፤ እንደሚሳካልህ እንጅ እንደምትወድቅ አትመን!..... ራስህ ለመቀየር ካሁን ጀምር!
ክፍል ሁለት ሁለተኛውን የስኬት እርከን ይዞ ይቀጥላል፤

“እችላለሁ” ወይም “ይሳካልኛል” ብሎ ማሰብ የስኬት የመጀመሪያ ደረጃ እንዲሁም ዕምቅ ሀይላችንን አንድንጠቀምበት የሚያስችለን ስለሆነ በዚህ ጉዳይ ላይ በደንብ እንወያይበት፤ ሁላችንም ግንዛቤ ውስጥ አስገብተን እንድንጠቀምበት በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰማንን እንግለጽ፤ ጥንያቄ መጠየቅ ይቻላል፤ ሰልጠና ስለሆነ እንያንዳንዱ ነገር በደንብ እየተረዳነው መሄድ አለብን፤ እንዲሁም ስለኮርሱ አሰጣጥ አስተያየት ካለ እንቀበላለን፤
Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular