Today Awoliya

7ኛው ሳምንት ታላቁ የተቃውሞ ትዕይንት ተካሄደ!
by Zain Usman 
ለ7ኛ ጊዜ ቀጥሎ የዋለው የህዝበ ሙስሊሙ ትዕይንተ-ተቃውሞ በአወሊያ ተካሂዶ ዋለ፡፡ ከመቼውም ጊዜ እጅግ የላቀ የህዝብ ቁጥር ያስተናገደው ይህ ትዕይንት በሠላማዊ መንገድ ተጠናቋል፡፡ ከክልል ከተሞች ሳይቀር የመጡት ሙስሊሞች ትዕይንቱን ለመታደም ወደ አወሊያ መትመም የጀመሩት ገና በማለዳ ሲሆን ከቀኑ አምስት ተኩል አካባቢ ግቢው እጅግ ተጨናንቆ ጣት ማሣረፊያ ቦታ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡የትዕይንቱ ተሳታፊ በመመስል በታዳሚው ውስጥ ሰርገው በመግባት ትዕይንቱን የማደፍረስ ተልዕኮ ይዘው የመጡ ግለሰቦች ሊኖሩ እንደሚችሉና ህዝቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚያውጅ መልዕክት ከመድረክ በኩል ከተላለፈ በኋላ መድረኩን ታዋቂው ዳዒ ኡስታዝ ባሕሩ ዑመር ተረክቦ ጠቃሚ እና ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር ቀጥተኛ ዝምድና ያላቸውን ቁም ነገሮች ለህዝቡ እያካፈለ የኹጥባው ሠዓት ደረሰ፡፡ የሸኽ ዑመር /የመስጂዱ ኢማም/ ኹጥባን ተከትሎ የዕለቱ ዝግጅት በተከታታይ ተክቢራዎች በመታጀብ መጀመሩ ይፋ ከተደረገ በኋላ የዕለቱ ፕሮግራሞች ተዋውቀው መድረኩ ተከፈተ፡፡  የህፃን ሪሃና ‹‹መኖሬን ጠላሁት›› ግጥም እድምተኛውን እንባ አራጭቷል፡፡የራያ አባ ሜጫ የመንዙማ እንጉርጉሮ የሚፈለገውን መልዕክት ከማስተላለፍ ጋር በተያያዘ የህዝቡን ቀልብ መግዛት ችሏል፡፡ በዕለተ ረቡዕ ምሽት በራዲዮ ፋና 98.1 የተላለፈው ፕሮግራም አብዛኛው ሙስሊም እንደተከታተለው ግምት ተወስዶ የተነዛውን የማደናገሪያ እና ውዥንብር የመፍጠሪያ ፕሮፓጋንዳ ለህዝብ ግልፅ ማድረግ ያስችል ዘንድ በወጣቱ የታሪክ ፀሀፊ አሕመዲን ጀበል በኩል ኪታባቸውን ይዞ እንደ መረጃ በመጠቀም እነኚህ አላህን የማይፈሩ ሰዎች የቀጣጠፉትን ትልቅ ውሸት አጋልጧል፡፡ ንግግሩን ‹‹ … ስለሆነም ጥያቄያችን በሚዲያ ‹ሹብሀ› በሚፈጥር መልኩ ቀረብም አልቀረበም የመጅሊስ መሪዎች ይወርዳሉ! ›› በማለት አጠቃሏል፡፡ ታዳሚውም በቀረበው የአህመዲን ዝግጅት በመርካት በተደጋጋሚ ተክቢራ አሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎ ሁለት አዋቂ ሴቶች አህባሽን በተመለከት ያዘጋጁትን ግጥም ለታዳሚው እንካችሁ ብለዋል፡፡ በጉጉት ይጠበቅ የነበረውና የየካቲት 5 ቀጠሮ ምላሽ የመቅረቢያው ሠዓት በመድረሱ የነበሩት 17ቱም ተመራጭ ኮሚቴዎች መድረክ ላይ ተጣዱ፡፡ ኮሚቴዎቹን በመወከል ኡስታዝ ካሚል ሸምሱና ኡስታዝ አቡበክር አሕመድ ተራ በተራ ሪፖርታቸውን አቀረቡ፡፡ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ የሪፖርቱን ዝርዝር ሀተታ ለኡስታዝ አቡበክር በመተው የውይይቱን አጠቃላይ አንደምታ እና  መልካም ገፅታዎች አብራርቷል፡፡ ኡስታዝ አቡበክር ያቀረበው የሪፖርት ይዘት ከሞላ ጎደል የሚከተሉትን ነጥቦች የያዘ ነበር፡፡
የህዝቡ ጥያቄ ይበልጥ መሠማት እንዲችል፣ ጉዳዩ ከዳር እስከ ዳር እንዲደርስና የሚመለከተው አካል በሙሉ እንዲያውቅ የተከበሩ ጠ/ሚንስትሩን ጨምሮ ለስምንት የመንግስት የሚንስቴር መስሪያ ቤቶች 7 ገፅ ያለው ጥያቄዎችን ያዘሉ ደብዳቤዎችን ማስገባታቸው፣ በድንገተኛ ችግር ምክንያት ከሁለት ሰዎች በስተቀር 15ቱ የኮሚቴ አካላት በፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ተገኝተው ከሚንስትሩ ጋር ውይይት እንዳደረጉ በዚህም፡- ሚንስትሩ እንደተናገሩት ፡-
‹‹ በቀጠርናችሁና ቃል በገባነው መሠረት ጉዳያችሁ መፍትሄ ያገኛል፣ምላሽ እንሰጣለን፣ምላሽ የማንሰጠውም ነገር ካለ በግልፅ እናሳውቃለን ››ማለታቸው፣ ‹‹ጥያቄያችሁን አሁንም ባለው አግባብ  መቀጠል ትችላላችሁ›› ማለታቸው፣ ‹‹ጥያቄዎቻችሁ በሙሉ ግልፅ ናቸው ጥያቄዎቻችሁን በሙሉ ተረድተናል፣ገብቶናል›› ማለታቸው የመጨረሻውን ውሳኔ ለመስጠት ለየካቲት 26 ቀጠሮ መሰጠቱ፣ ለየካቲት 26 የመጨረሻና ሁሉንም የሚያስደስት ምላሽ እንሰጣለን ማለታቸውን፣ ያኔ ምላሽ ካልሰጠን ምላሽ አልተሰጠንም ስትሉ የምትፈልጉትን ማድረግ ትችላላችሁ በማለት ቃል መግባታቸውን አብራርቷል፡፡ (ኡስታዝ አቡበክር ይህንን ሲናገር ህዝቡ የማያባራ ተክቢራ አሰምቷል) በመጨረሻም እስከ የካቲት 26 ድረስ ሁላችንም በትዕግስት በመጠበቅ ጠ/ሚንስትሩን ጨምሮ ደብዳቤ ያስገባንላቸው የመንግስት አካላት በጥልቅ ተወያይተውበት አፋጣኝ ምላሽ እንደሚሰጡን ተስፋ እናደርጋለን፣ እኛም በትዕግስት እንጠብቃለን፡፡ኢንሻ አላህ! በማለት ንግግሩን አጠናቋል፡፡
የህዝቡ የተክቢራ ጩኸት ማባሪያ አልነበረውም፡፡ ታዳሚው በሁኔታው እጅግ የተደሰተ ይመስላል፡፡
ወደ ፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ የአጭር ደቂቃ እድል ተሰጥቶት የነበረው ኡስታዝ ያሲን ኑሩ ከሚንስትሩ ጋር በነበራቸው ቆይታ ያስታወሳቸውን ሦስት ጠቃሚ ነገሮች እነሱም፡-
መጅሊስ ሰፊውን ህዝብ እና ወኪሎቻቸውን  ፅንፈኛ፣ አሸባሪ… እያለ በየመድረኩ የሚናገረውን ንግግር እና የሚለጥፋቸውን ማስታወቂያዎች እንደሚቃወሙና ከዚህ በኋላ ባስቸኳይ እንዲያቆም እንደሚነግሯቸው ሚንስትሩ መናገራቸውን፣ እናንተን አሸባሪና አክራሪ ብሎ መወንጀል ከእናንተ ጋር ውይይት የሚያደርገውን መንግስትንም መወንጀል ስለሆነ እንደሚቃወሙ ሚንስትሩ መናገራቸውንና እስከ የካቲት 26 የመጨረሻ መልስ እስከሚሰጥ ድረስ እየተገናኘን መነጋገር እንድንችል ስልካችንን ተቀያይረናል ሲል ብስራት ያላቸውን ቃላት በቀልድ በማዋዛት እና ህዝቡን የቢላል(ረ.ዐ) መፈክር በመባል የምትታወቀውን ‹‹አሐዱን አሐድ!›› በማስባል መልዕክቱን ካስተላለፈ በኋላ መድረኩን ለቋል፡፡ የኡስታዝ ያሲን ኑሩ ንግግር የፕሮግራሙ መቋጫ ሆኖ በመድረኩ ቆይታ በተደጋጋሚ ሲነገር የቆየው ‹‹ሳምንት ጁምዓ በአወሊያ እንስገድ›› መልዕክት ተላልፎ የዕለቱ መድረክ በቁርኣን ንባብ ከተዘጋ በኋላ ቁጥር ስፍር የሌለው ኸልቅ በሰላም ወደ ቤቱ ተመልሷል፡፡
Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular