yederes leredio fana azegage

ይድረስ ለፋና 98.1 ጋዜጠኛው ብሩኬ
ውድ ብሩኬ መቼም የጋዜጠኝነትን ሀ ሁ ላንተ ማስቆጠር አልችልም ፡፡እምነቴም በማላቀው ነገር እንዳላወራ ማዕቀብ ጥሎብኛል፡ግን የአቶ አህመዲንን ንግግር ስታዳምጥ ተረት ተረት እንደምተወድ ተረዳሁና አንድ ተረት ጸፍኩልህ በውስጥ አንተን ታገኘዋለህና አንብበው 
አንድ ሞኝ አሽከር የነበረው ሰው ነበር አሉ፡፡ ይኼ አሽከር አድርግ የተባለውን ካልሆነ በቀር አስቦ፣ አውጥቶ እና አውርዶ፣ ብሎም አመዛዝኖ የሚሠራው ሥራ አልነበረም፡፡ ምን ጊዜም የሚጠብቀው የአለቃውን ትእዛዝ ብቻ ነው፡፡ ለእርሱ ትክክል ነገር ማለት ጌታው ያዘዘው ሲሆን፣ ስሕተት ማለት ደግሞ እርሱ ያልነገረው ነገር ማለት ነው፡፡ ዓላማው ጥሩ ነገር መሥራት ወይንም አዲስ ነገር መሥራት ሳይሆን አለቃውን ማስደሰት ብቻ ነበር፡፡
ጌታው ከሳቀ ይስቃል፣ ካለቀሰ ያለቅሳል፣ ከተደሰተ ይደሰታል፣ ካዘነም ያዝናል፡፡ የወደደውን ይወድዳል የጠላው ይጠላል፡፡ ለርሱ የመደሰቱንም ሆነ የማዘኑን፣ የመሳቁንም ሆነ የማልቀሱን ምክንያት ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ ዋናው ነገር ጌታው መሳቁ ወይንም ማልቀሱ ነው፡፡ አንዳንዴ ሰዎች የሳቀበትን ምክንያት ሲጠይቁት «ጌታው ሳቁኮ አላያችሁም» ይላል፡፡ በዚህም የተነሣ ሰዎች «እንዳሉት»ብለው ይጠሩት ነበር፡፡
አንድ ቀን ጌታው እና እንዳሉት ወደ መንገድ ወጡ፡፡ እርሱ በእግሩ ከኋላ እየተከተለ፤ ጌታው ደግሞ በፈረስ ከፊት እየበረሩ፡፡ መንገድ ላይ ጌታው የገንዘብ ቦርሳቸውን ጣሉት፡፡ እንዳለውም ቦርሳውን አልፎት ሄደ፡፡ጌታው ያሰቡበት ከተማ ገብተው ኪሳቸውን እስኪቀደድ ቢበረብሩ ቦርሳቸውን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም ወደ እንዳሉት ተጠጉና «የገንዘብ ቦርሳ አላየህም» አሉት፡፡ እንዳሉት «አይቻለሁ፣ መንገድ ላይ ጥለውታል» አላቸው፡፡ 
ጌታው ደንግጠው እና ተናድደው «ታድያ ለምን አንሥተህ አልሰጠኸኝም» አሉት፡፡ እንዳሉት ደንግጦ አሰበ፣ አሰበ፣ አሰበ፡፡ ግን የተሰጠው መመርያ አልነበረም፡፡ ተከተለኝ ከማለት በቀር የነገሩት ነገር አልነበረም፡፡ «እንዴ እርስዎ የገንዘብ ቦርሳዬ ሲወድቅ አንሥተህ እንድትሰጠኝ መች አሉኝ» አላቸው፡፡ እርሳቸውም «በል ከዛሬ ጀምሮ እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካየህ ሰብስበህ እንድትሰጠኝ» አሉት፡፡ ከእሺ በቀር ሌላ የማያውቀው እንዳሉት በጸጋ ተቀበለ፡፡ በቀጣዩ ጊዜ ጌታውን ተከትሎ መንገድ ጀመረ፡፡ መመርያው በልቡ ነበር፡፡ የሚያሳስበው የተነገረው ነገር ነው፡፡ በልቡ ውስጥም ከተነገረው ነገር በቀር ምንም ሌላ ነገር አልነበረም፡፡ የርሱ ልብ አዲስ ነገር አያመነጭም፤ አዲስ ነገር ማመንጨት የሚችሉት የርሱ አለቃ ብቻ ናቸው፡፡ የርሱ ሥራ ያለ ጥርጥር ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት ማለት ብቻ ነው፡፡ ለምን? ማለት አያውቅም፡፡ ለምን? ማለት ከጀመረማ አሽከር አይሆንማ፡፡ አሽከር ደግሞ ይጠይቃል? ይጠየቃል እንጂ? አሽከር ደግሞ ያስባል? ይታሰብለታል እንጂ? አሽከር ደግሞ ይመረምራል? ይመረመራል እንጂ? አሽከር ደግሞ ይገመግማል? ይገመገማል እንጂ? አሽከር ደግሞ ያፈልቃል? ይፈልቅለታል እንጂ? ምን ሲባል፡፡ እናም ተከትሎ ሄደ፡፡ የታዘዘው ትእዛዝ ብቻ ነበር ትዝ የሚለው፡፡ «እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካገኘህ ሰብስበህ እንድትሰጠኝ» የሚለው፡፡ ይህ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ አንዳች ነገር እንዲወድቅ ተመኘ፡፡ ያለበለዚያማ ትእዛዝ ፈጻሚ ላይሆን ነው፡፡ የሚወድቅ ነገር ከሌለማ እርሱ የወደቀን ሰብሳቢ መሆኑ እንዴት ይታወቃል? ስለዚህ ለመሰብሰብ ሲባል ብቻ መጣል አለበት፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ አንዳች ነገር መውደቅ ጀመረ፡፡ እርሱም እያነሣ በቀረጢት ከተተ፡፡ ሲወድቅ ሲያነሣ፣ ሲወድቅ ሲያነሣ፣ ሲወድቅ ሲያነሣ በመጨረሻ ያሰቡበት ቦታ ደረሱ፡፡ አለቃውም «እህሳ፣ ዛሬስ የወደቀ ነገር የለም?» አሉት፡፡ «አለ እንጂ» አላቸው፡፡ ደንግጠው ኪሳቸውን ዳበሱት፡፡ ቦርሳቸው ከነገንዘቡ እንዳለ ነው፡፡ 
«ምንድን ነው የወደቀው?» አሉት ጌታው፡፡ እንዳሉት ግን ቀረጢቱን ይዞ መጣ፡፡ ሲከፍተው የፈረሱ ፋንድያ ነበር፡፡ አለቃው ተናደዱ ፡፡ 
«ይህንን ምን ሊጠቅምህ ሰበሰብከው?» አሉትም፡፡
«እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካገኘህ ሰብስብ ብለውኛላ» አላቸው፡፡ እውነቱን ነው፡፡ አሽከር አንድ ነገር ይጠቅማል፣ አይጠቅምም፤ ያስፈልጋል፣ አያስፈልግም ብሎ እንዲወስን ማን ፈቀደለት? አሽከር ማለት የታዘዘውን ብቻ የሚፈጽም ማለት ነው፡፡ አሽከር ከአንገት በታች እንጂ ከአንገት በላይ አለው እንዴ? ከአንገቱ በላይ ያለው ከአለቃው ዘንድ ነውኮ፡፡
«በል» ከዛሬ ጀምሮ የምታነሣው ቦርሳዬ፣ ካባዬ፣ ባርኔጣዬ፣ ጅራፌ፣ ገንዘቤ፣ እንዲሁም ከፈረስ ዕቃዬ አንዱ ነገር ከወደቀ ብቻ ነው»፡፡ እንዳሉት በፈገግታ ተቀበለ፡፡ ግን ፈራ፡፡ ይህንን ዝርዝር ቢረሳውስ፡፡ ቁጭ ብሎ በአንድ ወረቀት ላይ ጻፈው፡፡ መጻፍ ብቻ አይደለም እንደ ደጋገመው፡፡ በሄደበት፣ በተቀመጠበትም ይህንኑ ዝርዝር ብቻ ነበር የሚናገረው፡፡ ሰው ለሚጠይቀው ማናቸውም ነገር መልሱ ይሄ ዝርዝር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ዝርዘሩን የሰጡት አለቃው ናቸዋ፡፡
ከሰዎች ጋር ሲያወራ በየንግግሩ ጣልቃ ዝርዝሩን ማንሣት አለበት፡፡ አብረውት የሚያወሩት ሰዎች ግራ ይገባቸዋል፡፡ ለርሱ ግራ ቢገባቸው፣ ቀኝ ቢገባቸው ግዱ ነው፤ ዋናው የአለቃውን ትእዛዝ አለመርሳቱ፣ እርሱንም የንግግሩ ማሟሻ ማድረጉ ነው፡፡ እርሱ ዋጋውን ከአለቃው እንጂ ከሕዝቡ አልያም ከህሊናው አያገኝ፡፡ ሌሎች ሰዎች ቢወዱት እንጂ አይሾሙት፤ ቢያደንቁት እንጂ አያበሉት፡፡ እንጀራውም ሹመቱም ያለው በአለቃው ዘንድ ነው፡፡
ለሦስተኛ ጊዜ መንገድ ተጓዙ፡፡ እንዳሉት እና አለቃው፡፡ በሄደበት መንገድ ሁሉ የሚጓዝበትን አካባቢ፣ ዛፎቹን እና እንስሳቱን፣ መንደሩን እና መስኩን አያይም፡፡ እየደጋገመ የሚያየው ዝርዝሩን ነው፡፡ አንዴ ዝርዝሩን፣ አንዴም መንገዱን ያያል፡፡ ከዝርዝሩ መካከል መሬት የወደቀ እንዳለ ብሎ፡፡ 
እርሱም ዝርዝሩን እንዳየ አለቃውም እንደሸመጠጡ ያሰቡበት ቦታ ደረሱ፡፡ 
«እህሳ ዛሬስ የወደቀ ነገር አለ?» አሉት፡፡ «የለም፤ ከዝርዝሩ ውስጥ የወደቀ ነገር የለም» አላቸው፡፡ ለእርሱ ዋናው የሚጠቅም ነገር ወድቋል? የሚለው አይደለም፤ ከዝርዝሩ መካከል፤ ከታዘዘው መካከል ወድቋል ወይ? የሚለው ነው፡፡ ከዝርዝሩ ውጭ ምን ነገር አለ? ማንኛውም ነገር ያለው በዝርዝሩ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከዝርዝሩ ውጭ ያለ ነገር አንድም እንዳለ አይቆጠርም፤ ያለበለዚያም የማይጠቅም ነገር ነው፡፡ ዋናው ዝርዝሩ ነው፡፡ እናም 
ደስ አለው፡፡ ከዝርዝሩ መካከል የነጠበ ነገር የለምና፡፡ 
«ዝርዝሩን ይጠብቅልን» ብሎ ጸልዮ ተኛ፡፡ ያለ ዝርዝሩ እንዴት መኖር ይቻላል፡፡
ከብዙ ጊዜ በኋላ እንዳሉት እና አለቃው ለአራተኛው ጉዟቸው ተነሡ፡፡ እርሳቸውም ፈረሳቸውን እርሱም ዝርዝሩን አዘጋጁ፡፡
ሄዱ፡፡ ሸመጠጡ፡፡ እርሳቸው ፊት ፊታቸውን፣ እርሱም ዝርዝሩን እያዩ፡፡ ዋናው ዝርዝሩ ነው፡፡
ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ
መንገድ ላይ ፈረሱ አደናቀፈውና አለቃውን ይዟቸው ወደቀ፡፡ ፈረሱም የሲቃ ድምጽ አሰማ፡፡ ጌታውም ጮኹ፡፡
«አንሣኝ አንሣኝ» እያሉ ጮኹ አለቃው፡፡
እንዳሉት ዝቅ ብሎ በእጁ ያለውን ዝርዝር አየ፡፡ አለቃውን ሲወድቁ እንዲያነሣ የሚያዝ በዝርዝሩ ውስጥ የለም፡፡
«አላነሣዎትም» አላቸው፡፡
«ለምን ለምን፤ ኧረ ተላላጥኩልህ አንሣኝ» አሉት በልመናም በትእዛዝም፡፡
«የለም አለቃው በዝርዝሩ ውስጥ እርስዎ የሉም»
በመካከል ፈረሱ ተነሣ፡፡ አሽካካ፡፡ አለቃው ግን ሰውነታቸው ተላልጦ እየደማ እዚያው ያቃስቱ ጀመር፡፡
ፈረሱ መንገዱን ይዞ ሸመጠጠ፡፡ አለቃው እጃቸውን እያርገበገቡ «እባክህ ስለ ፈጠረህ አምላክ አንሣኝ» እያሉ እንዳሉት ለመኑት፡፡ እርሳቸው ያንን ዝርዘር ሲሰጡት ቃላቸውን ለማስጠበቅ እና ከቃላቸው እንዳ ይወጣ እንጂ እርሳቸው ሊወድቁ እንደሚችሉ መች ገመቱ፡፡ ደግሞስ አለቃ እወድቃለሁ ብሎ እንዴት ይገምታል፡፡ አለቃ አይደሉ፡፡
አሁንም እጃቸውን እያርገበገቡ ለመኑት «አንሣኝ አንሣኝ እባክህ» እንዳሉት ግን ፈረሱን ተከትሎ አሁንም ዝርዝሩን እያየ ትቷቸው ሮጠ፡፡
ብቻውን «እንዴ እዚህ ዝርዝር ውስጥ የሌሉትን እንዴት ብዬ ላንሣቸው፡፡ በኋላ ደግሞ ከዝርዝሩ ውጭ አነሣህ ብለው ራሳቸው ቢቆጡኝስ፡፡ እኔ ካዘዙኝ ውጭ ሠርቼ ዐውቃለሁ? አሁን ማንን ክፉ ለማድረግ ነው» እያለ እያጉረመረመ ፈረሱን ተከትሎ ነጎደ፡፡ብሩኬ በአንተና በእናዳሉት መካከል ምን ልዩነት ያለ ይመሰልሀል?ስማችሁ ብቻ ነው የሚለያየው አይደል ?ካልተቀየምከኝ እኔም እንዳሉት አልኩህ፡፡ 
“እውነት በዶዘር ቆፍረው ብትቀብርዋትማ አንድ ቀን በአካፋ ቆፍራም ቢሆን መውጣትዋ አይቀርም”
  • sebrina

    ለእንዳሉና ለመስሎቹ ትልቅ ትምህርት ነው፡፡እውነት ዪዘገያል እንጂ ........?!

Related Articles

Latest Articles

Most Popular