WHAT IS DIABETES

የስኳር በሽታ ምንድን ነው? ምልክቶቹና መፍትሄው!!!

 

 

 

አንድ ሰው የስኳር በሽተኛ ነው የምንለው በሰውነቱ ውስጥ የሚገኘው የደም ግሉኮስ(ስኳር) በጣም ሲጨምር ሲሆን ይህም ሊከሰት የሚችለው አንደኛ የሰውነታችን የኢንሱልን የማምረት ብቃት በቂ ሳይሆን ሲቀር፣ ሁለተኛው ደግሞ ሰውነታችን የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መቀበል ሳይችል ሲቀር ወይም ሁለቱም ባንድ ላይ ሲከሰት ነው።
እዚህ ላይ ኢንሱሊን ምንድንነው ብላችሁ ካላችሁ፡ ምግብ ስንበላ ሰውነታችን ምግቡን ወደ ስኳር ይቀይረዋል፤ በዚህ ሰዓት የሰውነታችን ጣፊያ (pancreas) ኢንሱሊን የሚባለውን ነገር ያመነጫል፤ ይህ ኢንሱሊን የሰውነታችን ህዋሶች እንዲከፈቱ በመርዳት የተመረተው ግሉኮስ (ስኳር) ወደ ውስጥ እንዲገባ በማድረግ ለሀይል ምንጭ እንድንጠቀምበት ይረዳል።
በዓለምአቀፍ ደረጃ በአሁኑ ሰዓት 380 ሚሊዮን ህዝቦች በስኳር በሽታ ተይዘው ይገኛሉ። የዓለም ጤና ድርጅት እንደገመተው ከሆነ በ 2030 ይህ ቁጥር በእጥፍ ይጨምራል። ባለንበት ጊዜ የስኳር በሽታ የሚያጠፋው ነፍስ በኤድስና በጡት ካንሰር ሕይወታቸው የሚያልፍ ሰው ተደምሮ ይበልጣል።
ከሌሎች በሽታዎች በበለጠ የስኳር በሽታ ለአይነ ስውርነት, የኩላሊት ሥራ ማቆም እና ለልብ በሽታ ዋና መንስኤ ሆኖ ይገኛል።
ሁለት አይነት የስኮር በሽታ አይነቶች አሉ፦
1. አይነት አንድ (Type 1) የስኳር በሽታ
በጣም ከባዱ የስኮር በሽታ አይነት ሲሆን ከኢንሱሊን አመራረት ጋር የተያያዘ ነው። አብዛኛውን ጊዜ የሚከሰተው በሕጻንነትና በጉርምስና (teenager) ጊዜ ነው። ሆኖም ግን በሌላ የእድሜ ክልል ውስጥ አይከሰትም ማለት አይደለም።
በዚህ አይነት የስኳር በሽታ ላይ የሰውነታችን አሰራር የራሱን ጣፊያ የሚያጠቃበት ሁኔታ አለ። ተመራማሪዎች ለምን እንደሆነ እስካሁን እርግጠኛ ባይሆኑም የሰውነታችን የመከላከሊያ ስርዓት (immune system) በስህተት በጣፊያ ውስጥ የሚገኙትን ኢንሱሊን የሚያመርቱ ህዋሶች እንደውጭ አካል በመመልከት ያጠፋቸዋል። ኢንሱሊን የለም ማለት ደግሞ የስኳር ክምችት ጨምሮ ወደ ግሉኮስ ሳይቀየር ይቀርና ሰውነታችን የሚያስፈልገውን ግሉኮስ ሳያገኝ ይቀራል። በህክምና ካልታዩት ይህ የበዛ የስኳር ክምችት አይንን፣ ኩላሊት፣ ነርቭን እና ልብን በመንካት ሞት ድረስ የሚደርስ አደጋ ሊያደርስብን ይችላል።
2. አይነት ሁለት (Type 2) የስኮር በሽታ
ሁለተኛው አይነት የስኳር በሽታ ደግሞ ከኢንሱሊን ጋር ብዙም ያልተያያዘ ሲሆን ብዙውን ጊዜ የሚያጠቃው ከ35 ዓመት በላይ ያሉ ጎልማሶችን ነው። በዚህ በሽታ የተጠቁ ህመምተኞች ከፊሉን ለሰውነታቸውን የሚያስፈልገውን ኢንሱሊን ማምረት የሚችሉ ሲሆን ችግሩ ብዙውን ጊዜ የኢንሱሊኑ መጠን በቂ ሆኖ አለመገኘቱ ነው። ቅድም እንደተገለፀው ኢንሱሊኑ የሰውነታችንን ህዋሶች በመክፈት ግሉኮስ እንዲገባ ሙከራ ቢያደርግም አይሰራም። አብዛኛውን ጊዜ በዚህ የሚጠቁት ከሚፈለገው በላይ ክብደት ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜ እንደ ስፖርትና የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር መከላከል ሊቻል ይችላል። በዘር የሚተላለፈው የስኳር በሽታም እዚህ ውስጥ ይመደባል።

የስኳር በሽታ ምልክቶች

ቶሎ ቶሎ ሽንት መምጣት
ከባድ የሆነ ጥማት
ከባድ የሆነ ራብ
ድንገተኛ የክብደት መጨመር
ድንገተኛ የክብደት መቀነስ
የተቆረጠ ወይም የተቀደደ የሰውነት ክፍል ቶሎ አለመዳን
ስሜት አልባ መሆን
የእይታ መጠን መቀነስ (ብዥ ማለት)

የስኳር በሽታ መከላከያ መንገዶች 
ክብደታችንን መከታተል
እንቅስቃሴ (ስፖርት) መስራት
የተስተካከለ የአመጋገብ ስርዓት መኖር
ከካፌ ወይም ሬስቶራንቶች የሚወጡ 'ቴክ አዌይ' አለማብዛት (ቤት ውስጥ አዲስ (fresh food) ነገሮችን መስራትና መጠቀም)
መጠጥ ማቆም 
ማጨስ ማቆም 
የደም ግፊትን መከታተል
በየጊዜው በዶክተር መታየት (check up)
በአጠቃላይ የአኗኗር ዘይቤያችንን ጤነኛ ወደ ሆነ መንገድ መቀየር

ሳይንስና ቴክኖሎጂ መረጃ ማዕከል