“አንድ ሀገር ብዙ ኃይማኖት” በሚል ርዕስ የተላለፈው ዘጋቢ ፊልም እንዳበሳጫቸው በቀረፃው የተሳተፉ ምሁራን ገለፁ


አዲስ አበባ ሬዲዮ ቢላል ሰኔ 26/04

          ትላንት ምሽት “አንድ ሃገር ብዙ ሃይማኖት” በሚል ርዕስ በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተላለፈው ፕሮግራም ለሀሰት ፕሮፖጋንዳ እንዲመች ተደርጎ መቅረቡ እንዳበሳጫቸው በቀረፃ የተሳተፉ ኡስታዝ ሃሰን ታጁና አህመዲን ጀበል ገለፁ፡፡

          ኡስታዝ ሃሰን ታጁ የፕሮግራሙን መተላለፍ ተከትሎ ዛሬ በሰጡት አስተያየት ከፕሮግራሙ አጠቃላይ ይዘት ሶስት ዓላማዎችን መገንዘብ ችለዋል፡፡

 

          የመጀመሪያው በኢትዮጵያ አክራሪነት የሚለውን ለማሳየት ፣ሁለተኛ ኃይማኖታዊ ተቋሞች ላይ ጥያቄ የሚያነሱና የሚቃወሙ አክራሪዎች መሆናቸውንና የአክራሪነት መገለጫ መሆኑን የማሳየት ዓላማ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ደግሞ በአወሊያ እየተካሄደ ያለው ሰላማዊ የሙስሊሞች ተቃውሞ ህገ-ወጥ እንደሆነ ለማሳየት መሆኑን እንደታዘቡ ነው ኡስታዝ ሀሰን ተጁ በፌስ ቡክ የሰጡት አስተያየት የሚያመለክተው፡፡

ለኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ጋዜጠኛም ስልክ በመደወል የተሰራው ፕሮግራም እጅግ አሳፋሪና ከአንድ ሙያተኛ የማይጠበቅ መሆኑን እንደገለፁለት ጋዜጠኛውም ከቁጥጥሩ ውጪ የሆነ ነገር እንዳለበት መናገሩን አስታውቀዋል፡፡

          ከአራት ወራት በፊት ስለኃይማኖት መቻቻል በቴሌቭዥን ጣቢያው ጋዜጠኞች ቃለ ምልልስ መስጠታቸውን ያስታወሱት ኡስታዝ ሐሰን ታጁ፡-ለ2፡30 የሰጡት ማብራሪያ ለአምስት ደቂቃ ብቻ ተቀንጭቦ ለፕሮፖጋንዳ እንዲመች ሆኖ መቅረቡ እንዳሳዘናቸው ጠቅሰዋል፡፡

          በተመሳሳይ ከመካነ ሰላም የተጠየቀችውና ሁለት ኒቃብ የለበሱ እህቶች የሰጡት አስተያየት ከ3 ሰዓት በላይ የተቀረፀ ቢሆንም የተላለፈው ከሁለት ደቂቃ እንደማይበልጥ አመልክተዋል፡፡

          ባለፈው የካቲት ወር ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና መቻቻል ዘጋቢ ፊልም ለመስራት ሀሳብህን እናካት በሚል ከኢቲቪ ጋዜጠኞች ጋር ቀጠሮ ይዞ በመኖሪያ ቤቱ የ2 ሰዓት ከሩብ መቀረፁን የተናገረው ኢስላማዊ ታሪክ ፀሀፊው አህመዲን ጀበል ነው ፡፡

ከመብት ጋር በተያያዘ የተነሱትን ጥያቄዎች ከአክራሪነት ጋር ለማያያዝ መሞከሩ ግርምትን ጭሮብኛል ያለው አህመዲን ጀበል እውነቱን ካልተነጋገርን የእውነት መቻቻል ይመጣልን ሲልም ጠይቋል፡፡

Be the first to comment

Related Articles

Latest Articles

Most Popular