ye mejlis mercha ke gelobal wede mazegaja

የመጂሊስ ምርጫ፡ ከ’ግሎባል’ ወደ ‘ማዘጋጃ’ በ 2001 ፤ የቀድሞ መጂሊስ ሹማምንት የእነ አቶ ኤሊያስን ቡድን እንዝላልነት ለማረምና ሙሰኞችን ለፍርድ ለማቅረብ በሚል ህቡዕ ሰበብ በግሎባል ሆቴል በተሰየሙ ጉባዔተኞች አድስ ፤ታማኝና የአህባሽ ጥምቆች (ቅምጦችም ይሆናል- የፖለቲካ)፤ አረንጓዴ ጠምጣሚዎች አቶ አህመድን ጨሎን ራስ አድርገው፡ ሌሎች ደግሞ በተዋረድ ተሹመው (ተመርጠው አላልኩም) በጓሮ በር ወንበሩን ያዙ፡፡ እኛም ከዛሬ ነገ አቶ ኤሊያስ በ50 ሚሊዮን ብር ሙስና ተከሶ ፍርድ ቤት ሲቆም (ወይም ሲቀመጥ) ለማየት በጉጉት ስንጠብቅ፡ ስንጠብቅ …. (የዋሆች!) ተረስቶ ቀረ- ወይ አለማወቅ! ለካስ ለመሾም ሙስና ዋነኛ መስፈርት ሆኖ ኖሯል! እነ ጨሎም ቢሮውንና ሙስናውን ከተላመዱ በኋላ ከመንግስት ’አህባሽ’ን የማጥመቅ ዘመቻ እንደ ዋና የቤት(ቢሮ)ስራ ተሰጥቷቸው ተረከቡ፤ ከዚያም ቅደመ-ማፅዳት ስራ ጀመሩ-‘IIRO’ን ማስባረር፡ አወሊያን መረከብ፡ ለመንግስት መረጃ ማቀበል፤ የሙስሊሙን የልብ ትርታ መለካት ወዘተ…. ስንቱ ጥፋት ይዘረዘራል.. በመጨረሻም ከሊባኖስ 200 የአህባሽ ዓሊሞችን በማስመጣት በሃምሌ 2003 በሐረር ማጥመቁን በይፋ ጀመሩ ቀጥሎ በሌሎችም ቦታዎች አፋፋሙት፡፡ ህዝበ-ሙስሊሙም ነገሩን በሹክሹታ፤ በፊት-መፅሃፍ(facebook)ጫካ፤ በጋዜጣና መፅሄቶች መቃወሙን ተያያዘው፡፡ ተቃውሞው በውጭ ሃገራት አይሎ ነበርና በ November 21, 2011 በአሜሪካ የተቃውሞው ሰልፍ ፈነዳ፡፡ በሀገር ውስጥ ግን ፍርሃት እንደነገሰ ነው ሆኖም በታህሳስ ወር መጨረሻ ላይ የአወሊያ ኮሌጅ መዘጋትና መምህራንና ኢማም መባረርን ተከትሎ በጀግኖች የአወሊያ ተማሪዎች አገር ውስጥም የተቃውሞ ሰልፍ ፈንዳ፡ አድሳባዎችም አጎራባቾችም ሆኑ ክፍለ-ሀገሮች ከቤታችው፤ የፊት-መጽኃፍ ታጋዮችም ከጫካው በመውጣት የተቃውሞ ትግሉን ተቀላቀሉ፡ የቅሬታ ፊርማም ተጧጧፈ፤ ጥያቄውም ከአወሊያ ጉዳይ ወዴ መጂሊስ ይውረድ አደገ፤ መጂሊሶችም ጨነቃቸው፡ ተቃውሞውም ጠነከረ፡ በኮሚቴ ተዋቀረ፡ ወደ ክፍለ-ሀገርም ተሰራጨ ሀገራዊም ሆነ፤ እስካሁን የተዋጣለት አካሄድ መሄድ ችሏል፤ ከመቼውም በላይ አንድነት ጠንክሯል፤ ድጋሜ ላይላላም ተማምለዋል፤ አንዋር መስጅድ ላይ ከትሟል፤ መንግስትንም አወዛግቧል፤ ዓለምንም አስተጋብቷል፡፡ በጀት ለ2004 መጂሊስም በጥር ወር ላይ የ2004 አመታዊ በጀቱን ይፋ አደረገ፡ 636 ሚሊዮን ብር (“ከየት መጣ?” ብሎ መጠየቅ ያስቀስፋል) ለአወሊያም 6 ሚሊዮን ብር ስለተመደበለት ሰልፉን ትታችሁ ወደ ቤታችሁ ግቡ ተባለ (አይ መደለያ!!) ጋዜጣም ተገዛ(“አል-ቁድስ”)፡ በቅርቡም የሀገር ውስጥ ዊኪሊክሰ ይፋ አንዳደረገው ከበጀቱ ውስጥ 203ሚሊዮን ብር የሚሆነው በአቶ ጨሎ ልጅ የግል ቁጠባ ሂሳብ መግባቱን ፤ ለ”አል-ቁድስ” ጋዜጣ በየወሩ 88ሺህ ብር መሰጠቱን፤ አብዛኛው ገንዘብ ለአህባሽ ስልጠናና ለጫት ወጭ እንደሚውል መታቀዱን ሰማን- ጆሮን አትስማ አይሉት፡፡ የጉልቻ ለውጥ ዜና አሁንም እንዴ ሀገር ውስጥ ዊኪሊክሰ መረጃዎች መሰረት ባለፈው ሀሙስ ሚያዚያ 19 ቀን እጅ….ግ መራር ዱብዳ ከአቶ መለስ በፀጥታ አማካሪያቸውና የቀድሞ የትግራይ ክልል ብረትዘንድአንት(ትርጉሙ-መሳሪያ በእጅህ ያለ) አቶ ፀጋዬ በርኸ እና በፌደራል ገዳዮች ሚ/ር ‘ሙፍቲ’ ሽፈራው ተ/ማሪያም በኩል መጂሊሶች ከስልጣናቸው በእንድ ወር ጊዜ ውስጥ እንዲወርዱ ተነገራቸው፤ መቼም ከስልጣንና ከጫት መነሳት ይከብዳል ይላሉ (የሚያውቁት) እናም የኦሮሚያና የአዲሳባ መጂሊሶች አለቃቀሱ አሉ፤ ምርጫም በሰኔ ወር እንደሚካሄድ ተነገራቸው (ለነገሩ ከአሁን በኋላ ምን ሊያደርግላቸው-እኛ ከወረድን ሰርዶ አይብቀል ነውና ነገሩ!)-በፌደራል ገዳዮች ሚ/ር በጀትና መሪነት ብሎም በዑለማዎች ም/ቤት(በመጅሊሱ የተቋቋመ) ሽፋንነት- ልጅ አባቱን ሲመርጥ!! ይህን ዜና ተከተሎ ትላንት ግንቦት 1 ቀን በአድሳባ ማዝጋጃ ቤት አዳራሽ የ”ነባሩ” እስልምና ተከታዮች (ለአህባሽ በአቶ መለስ የተሰጠ አዲሱ ለምድ) ብቻ ለጉባዔ ታደሙ፤ መከሩም፤ ዘከሩም በመጨረሻ ላይ የእነ ጨሎ ልጅን ጅማሮ አጠናክሮ የሚቀጥል፤ ድክመታችውን የሚያርም፤ “ጊዜያዊ” የመጂሊስ ፕሬዜዳንት ለመሾም ጠንካራ ታጋይ ማፈላለጉን ተያያዙት፤ ከብዙ ቁፈሮ በኋላ አንድ ጀግና ብቅ አሉ-ከትግራይ(ዘረኛ እንዳትሏቸው-ዘረኝነት በኢስላም ቦታ የለውምና!) ሸህ ከድር ማህሙድ ይባላሉ፡፡ ሸህ ከድር የትግራይ ክልል መጅሊስ ፕሬዜዳንት የነበሩ ሲሆን ከወር በፊት ሚያዚያ 1 ቀን ስልጣናቸውን አስረከበው በታላቅ ሽኝት ለዕድገት ወደ አድሳባ መጥተው የዑለማዎች ም/ቤት ፕሬዜዳንት አማካሪ በመሆን ተሸመው ለአንድ ወር ያህል ካገለገሉ በኋላ ነው-ትላንት ለ”ጊዜያዊ” የፌዴራል መጅሊሰ ፕሬዜዳንትነት የታጩት(ጊዜያዊ በመጅሊስ ዘመን አቆጣጠር ገደብ የለውም)፡፡ ከአንድ ወር በኋላም ስልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል-ምናልባት ህዝበ-ሙስሊሙ ቁሞ ከጠበቃቸው! ይድረስ ለክቡር አቶ መለስ ከሁሉም በፊት አስቀድሜ በጨሎ ልጅ ቁጠባ ሂሳብ ውስጥ ያለውን 203 ሚሊዮን ብር እንዳይረሱት ለማስተወስ ነው-ስራ ስለሚበዛብዎት፤ ለነገሩ ምን አላትና እንደውም “አፍወቱል-አህባሽ” በሉት፤ ወይም ለተሰናባቾቹ እኩል ያካፍሏቸው፡፡ ክቡርነትዎ ሦስቶቹ መሰረታዊ ጥያቄዎቻችንን ቢያንገሸግሽዎትም እደገማቸዋለሁ.. 1. የመጅሊሳችንን መሪዎች እኛው፤ ከእኛው፤ ለእኛው፡ በነፃነት፤ በግልፅ፤ ያለማንም ጣልቃ-ገብነት በመሳጅዳችን እ…..ንምረጥ!!! ስለዚህ ‘ጥቁሩን አውርደው ነጩን አህባሽ(“ነባሩ” እስልምና አማኝ በራስዎ ቋንቋ እንዲገባዎት)ተኩልን’ በፍ…..ፁም ኧረ በፍ……ፁም አልንም፡፡ ምክንያቱም ጉልቻ ቢቀያይር ወጥ አያጣፍጥምና! ለነገሩ በቤተ-መንግስት ጉልቻ ስሌለለ ላይገባዎት ይችላል!!….ሰምተዋል!? መጅሊሱ በስንት አባቶቻችን ደም እንደተመሰረተ በአይንዎ አይተዋል! ደም፤ ህይወት፤ ገንዘብ፤ ጊዜና ጉልበት ተከፍሎበታል-ዛሬ ካዴሬዎች ቢፈነጩበትም! ስለዚህ በቃዎት፤ ጥላቻም ልክ አለው! በቃ……..! 2. አወሊያም ሆነ ሌሎች የሙስሊሙ ተቋሞችም እንደመጅሊሱ በብዙ መስዋዕትና ትግል የቆሙ ናቸው፤ ስለዚህ ለዚህ ለእርስዎ አድሱ(ውይ! ይቅርታ ተሳሳትኩ “ነባሩ”ማለቴ ነው) ሃይማኖት ማጥመቂያም ሆነ ለፖለቲካዎ ስራ መጠቀም አይቻልም፡፡ ሙስሊሙ እነደሰራቸው የራሱ ንብረት ሆነው በራሱ ሰዎች ይተዳደሩ!!! 3. አህባሽ ኢትዮጲያ ውስጥ ከ1994/5 ጀምሮ በ’NGO’ነት በራሱ ማዕከላት እንደሰበከው ዛሬም መስበክ ይችላል፤ ነገር ግን በእርስዎ ሰራዊቶች ተገደን፤ ተስፈራርተን በኢትዮጲያ ህዝብ ተቋማት ውስጥ ያለ አግባብ ሊጫንብን አይገባም፤ ነውርም ነው፤ ኢ-ሰብዓዊም ነው፤ ኢ-ህገ-መንግስታዊም ነው፤ ስለነባርነቱ ባይሰብኩን ይሻላል-ከፈለጉ እራስዎ ያምልኩት! የእኛን የእምነት ምርጫ ለእኛው ይተውልን!! ጥያቄዎቹ አለቁ፤ በቃ አራት ነጥብ(፡፡) አይጨመ(ም)ሩ፤ አይቀነ(ን)ሱ..(‘ጨ’ ና ‘ቀ’ ይጠብቃሉ!)- አራት ወራትን አሳለፉ!!! ስለዚህ ለሚያልፍ ቀን የማያልፍ ጥፋት አይስሩ! ጥቁር ታሪክ አይስሩ! ይድረስ ለሙስሊም ብሎም ለመላ ኢትዮጲያውያን ውድ ሙስሊም ወንድምና እህቶቼ፤ እናትና አባቶቼ ይህ ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄ ትግላችን ከፍተኛው ጡዘት ላይ ደርሷል-በአላህ ፈቃድ! በዚህም ሁለት ጥቁር ነጥቦች መቼም አይረሱንም-የካቲት 26 ፌዴራል ገዳዮች የተፋበት ቀን እና ሚያዚያ 19-የአሳሳ ንፁሃን ሙስሊም ወንድሞቻችን በፖሊሶች ጭፍጨፋ በግፍ ህይወታቸው ያለፈችበት(አላህ ጀነትን ያጎናፅፋቸው!) ቀን! ስለዚህ፤ 1. አሁንም ቢሆን አንድም ጥያቄያችን በአግባቡ አለመመለሱን በማወቅ ለሌሎችም በአግባቡ ማስረዳትና ሴራውን ማጋለጥ ብሎም ግንዛቤ በሰፊው መስጠት…. 2. አንድነታችንን በማጠንከርና ፍፁም ሰላማዊ በሆነና ከየመሳጅዳችን ቅጥር ግቢዎች ሳንወጣ የተቃውሞ ሰልፋችንን በበለጠ በማጠናክር ማካሄድ፤ (አደራ ስሜታዊ እናስወግድ) 3. የመንግስት ማስፈራሪያዎችንና ዛቻዎችን ከመጤፍ ሳንቆጥርና ቅንጣት ታክል ሳንፈራ በጥንቃቅ በመከታተል ራሳችን ለራሳችን የደህንነት ኃይል ሆነን በንቃትና በትጋት መጠበቅ፤ ለትልቁ ዓላማችን ወሳኝ ነውና፤ 4. ወደድንም ጠላንም ይህ ተቃውሞ ላይመለስ 11ኛው ሰዓት ላይ ደርሷል! ይህ ጥያቄ ከተቀለበሰ ትልቅ አደጋ አለው፤ ትልቅም ታሪካዊ ጠባሳ ጥሎ ማለፍም ብቻ ሳይሆን ምናልባት ላንዴዬና ለመጨረሻ ጊዜ ድጋሜ ላይነሳ ተቀብሮ ሊቀር ይችላል፤ ስለዚህ እንደ ቀላል ነገር ማየቱ እስልምናን በኢትዮጲያ ላይ አጣብቂኝ ውስጥ ከማስገባቱም ሌላ ለዚህም ተጠያቂዎቹ እኛው ነን!! 5. መረጃ ኃይል ነውና መረጃን በጊዜው፤ በዕውነተኝነት፤ በአስቸኳይ ለሌሎች ማቀበል፤ በትኩሱ መቀበልና ለክርስቲያን ወገኖቻችን ስለጉዳዩ ማስረዳት፤ ትዕይንቶችን በድምፅና በምስል በመቅረፅ ወደ ኢንተርኔት መረጃ ቋቶች መስቀል፤ ትዕይንቱንም በፅሁፍና በምስል መለጠፍና ለዜና አውታሮችም ማቀበል…ወዘተርፈ……….. በመጨረሻም ሁሉም ኢትዮጲያውያን ይህ ጉዳይ ከዘርፈ-ብዙዎቹ የኢህአዴግ የ”ከፋፍለህ ግዛ” አካል አንዱ ነውና ሴራውን ተረድተን ለመንግስት ፕሮፓጋንዳ ጀርባችንን ሰጥተን ሁላችንም ለወደፊቷ ኢትዮጲያ በአንድነት እንድንቆም፤ አንዱ አንዱን እንድጠብቅ (እንደ ግብፆቹ)፤ ከእያንዳድንዱ ሃይማኖታዊ ጥፋቶች ጀርባ የመንግስት ህቡዕ እጆች እንዳሉብት በማጤንና በመረዳት “በቃህ፤ ኧረ በቃ…..ህ” ልንለው ይገባል፤ ኧረ ህዝቦች- ኢትዮጲያ ጠፈች፤ በሀሰት ላይ ቆመች፤ ትውልዷ ከሸፈ፤ በጨካኞች ተሾፈረች፤ ስንቱ ….…… አንድ እንበላት!! ለዛሬ እኔ እዚህ ላይ ይብቃኝ፤ ትግሉ ግን ይቀጥላል!! ድል ለኢስላም ነው!! አሏሁ አክበር!! አሏሁ አክበር!! By Bin Moh
Be the first to comment

Latest Articles

Most Popular